ውል በማሰር የሚጀምረው አዲሱ የትምህርት ዓመት

Views: 155

በመላው ኢትዮጵያ በ2011 የመሰናዶ ትምህርታቸውን አጠናቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በ2012 ለሚቀላቀሉ ተማሪዎች ከወትሮው በተለየ ተቋማት አዲስ ገቢ ተማሪዎቻቸውን ከአንሶላ፣ ብርድ ልብስ እና ትራስ ልብስ ባለፈ ከሚኖሩበት አካባቢ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት በኩል የፈረሙትን ውል ይዘው እንዲመጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የሚገኙት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የእውቀት መገቢያነታቸው ተዘንግቶ ጎራ ተለይቶ መጠፋፊያ ቀጠና ሆነው የበርካታ ተማሪዎችን ሕይወት እንዲቀጠፍ የሆነበት ነበር።

ታዲያ ያለፉትን ዓመታት አለመረጋጋቶችና ግጭቶች በከፍተኛ ተቋማት ውስጥ ጭራሽ እንዳይከሰት በሚል በዘንድሮው ማለትም 2012 የትምህርት ዘመን አዲስ እና ነባር ተማሪዎች በሚማሩበት ዩኒቨርስቲ ውስጥ አስተዳደራዊ እና አካዳሚያዊ ሥነ ስርዓቶችን አክብረው ሊማሩ እና ሕገ ደንቦችን ጥሰው ቢገኙ ደግሞ ለሚወሰድባቸው ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ኀላፊነቱን ራሳቸው እንደሚወስዱ ውል እንዲገቡ ተደርገዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በዚህ ይብቃኝ ያለ አይመስልም። ወላጆችም ለጆቻቸውን በሚሔዱበት ዩኒቨርስቲዎች ያሉትን ሕጎች እንዲያከብሩ መምከራቸውን እና ተላልፈው ቢገኙ እና ለሚወሰድባቸው እርምጃ ልጆቻቸው ኀላፊነቱን እንደሚወስዱ አስታውቀው ውል ፈርመዋል።

በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ታዲያ በርካታ ግለሰቦች የውሉን ጠቀሜታ እያሞካሹ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እኩል በእኩል በሆነ ቁጥር ደግሞ በተቃራኒው በመቆም ተማሪዎች የሚያስሩት ውል ፋይዳው ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ትችታቸውን ሲያሰሙ ከፍ ሲልም ሲሳለቁ ነበር።

ተማሪዎች በተለይም ደግሞ አዲስ ገቢዎች ገና ከጅምሩ እንደዚህ ዓይነት ኀላፊነት ተሸክመው መግባታቸው ከትምህርት ውጪ ወደ ብጥብጥና ረብሻ የሚያመሩበት አዝማሚያ በእጅጉ ይቀንሳል፤ መንግሥት እንዲያውም ከዚህ ቀደም ያላሳየውን የኀላፊነት መንፈስ አሁን እየተገበረው ነው። ይበል የሚያሰኝ አካሔድ ነው ሲሉ ድጋፋቸውን ያለመሰሰት አስተጋብተዋል።

ከዚሁ በተቃራኒው የቆሙት ደግሞ የለም መንግሥት አሁንም ”የውሃ ቢወቅጡት” ዓይነት አካሔድ ነው እየተከተለ ያለው ዘንድሮም ለውጥ ለሌለው ጉዳይ ማወናበጃ እንጂ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም እንዲህ በቀላል የሚመለስ ሳይሆን ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተላልፈው ከተቋማት ውጭ ያሉት ውዥንብሮች ሲረግቡ ተያይዞ የሚረግቡ ናቸው ይላሉ። እንዲያውም ከጎረቤት በተለይም ደግሞ ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተገኘች ምክር መሆን አለባት ሲሉም የተሳለቁ አልታጡም። ቀጥለውም በወላጆች፣ በተማሪዎችና በትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በኩል የሚገባው ውል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ተማሪዎች ልብ ማሰሪያስ ይሆናል ወይ? በውል የሚመጣ ሰላም ካለስ እስካሁን መንግሥት ምነው ዘገየ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ከግራም ከቀኝም ሲናፈሱ ሰንብተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com