ለሀገር በቀል እውቀቶች የባለቤትነት መብት የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

Views: 688

ለሀገር በቀል እውቀቶች የሕግ ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው በመታመኑ ኅብረተሰቡ ለፈጠራቸው እና ላጎለበታቸው ሀገር በቀል እውቀቶች እና መድኀኒቶች የባለቤትነት መብት የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት፣ ማኅበረሰቡ በጊዜ ሒደት ያጎለበታቸውን እና ጠብቆ ያቆያቸውን ሀገር በቀል እውቀቶች ማኅበረሰቡ የባለቤትነት መብት የሚያገኝበትን እና የሕግ ከለላ እንዲያገኙ ለማስቻል የሚያግዝ አዋጅ አዘጋጅቶ ለእንዲፀድቅ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የማኅበረሰብን እውቀት ማስጠበቅ ለማኅበረሰቡ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት የአእምሯዊ ንብረት ሀብቶች አጠቃቀም እና የማኅበረሰብን ግንኙነት የተሻለ እንደሚያደርግ የታመነበት ረቂቅ አዋጁ የሀገር በቀል እውቀት ባለቤቶችን መብት የሚደነግግ ሲሆን አዋጁን ተላልፈው በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚወሰዱ የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ቅጣቶችን በውስጡ የያዘ ነው።

ረቂቅ አዋጁ በሀገር በቀል እውቀቶች፤ ትውፊቶች፤ የዘረመል ግኝቶች፤ ሀገር በቀል መድኀኒቶች አመዘጋገብ እና ዘረመል ግንኙነቶች እና ሀብቶች አጠቃቀም እንዲሁም የባለቤትነት መብቶችን በዝርዝር የሚይዝ ሲሆን በተዘጋጀው የማኅበረሰብ በቀል እውቀት አእምሯዊ ንብረት ረቂቅ ሕግ ላይ ሀገር በቀል እውቀቶቹ የባለቤቶችን መብት ሳይነካ ለትምህርታዊ ጥናት እና ምርምሮች የሚውሉበትን መንገድም የሚደነግግ ነው።

ማኅበረሰቡ በጊዜ ሒደት ያጎለበታቸውን እንደ ሙዚቃ፣ ባሕላዊ ውዘዋዜ እና መሰል እንቀስቃሴዎች በባለቤትነት በማስመዝገብ ለፊልም፣ ለሙዚቃ እና መሰል ዓላማዎች ባሕላዊ እወቀቱን የሚጠቀሙ አካላት በተዘጋጀ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ክፍያ እንዲፈፅሙ በማድረግ ማኅበረሰቡ ከባሕሉ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ የሚያመቻች እንደሚሆን ተገልጿል።

እንደ ብሩክ ኃይሌ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ንብረት ትምህርት ዘርፍ ምሁር ሐሳብ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በግል ደረጃ የፈጠራ አቅም ዝቅተኛ በሆነባቸው ሀገራት እንደ ሀገር የራሳቸውን ሀገር በቀል እውቀት፤ የቅጂ እና ተዛማጅ መብቶች እንዲሁም የፈጠራ ባለቤትነት መብቶችን ጠብቆ ማቆየት ተገቢ ቢሆንም በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን ያሉን በርካታ እና ሰፊ ሀገር በቀል እውቀቶች መጠበቅ ላይ ከፍተኛ ክፍትት መኖሩን ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገር በቀል እወቀቶች እና የዘረመል ሀብቶች ድንበር ተሻግረው ለፈጠራቸው እና ጠብቆ ላቆያቸው ማኅበረሰብ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በማያመጡበት መልኩ በሌሎች ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

እንደዚህ ዓይነት አዋጆች መዘጋጀታቸው ማኅበረሰቡ ራሱ በፈጠራቸው፣ ባጎለበታቸው እና ጠብቆ ባቆያቸው ሀገራዊ እወቀቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሞራል ጥያቄዎችን ለመመለስ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።

አዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ባሕላዊ መገለጫዎችን ለፈጠራቸው ማኅበረሰብ በባለቤትነት መስጠቱ ተግባራዊነቱ ላይ ችግር የሚፈጥር ይሆናል። ለአብነትም የአሸንዳ እና አሸንድዬ ባሕላዊ ትውፊቶች በአማራ እና በትግራይ ማኅበረሰቦች የሚከበሩ መሆናቸው እና ኹለቱም ክልሎች በኩል የባሕሉ ባለቤት ማነው የሚለው ጥያቄ በማኅበረሰቦቹ መካከል ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል ያነሳሉ።

እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን ለመፍታት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መሔዱን አልደግፈውም ያሉት ብሩክ ኃይሌ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ የባህል ግጭቶችን ለመፍታት የሚችልበት አግባብ በሕገ መንግሥቱ ላይ የለም ይላሉ ። ሆኖም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤትም ተወሰደ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻው ውሳኔ ሊሰጥ የሚገባው በሀገር በቀል እውቀቶች ሕግ መሆን አለበት ሲሊ ይገልፃሉ።

አገራችን በዓለም ዐቀፉ የንግድ ደርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ አእምሯዊ ንብረት ውጤቶችን የሚጠብቁ እና ለሀገር በቀል እውቀቶችን የሕግ ከለላ የሚያደርጉ ሕጎች መዘጋጀታቸው ሀገራችን በዓለም ዐቀፉ የንግድ ደርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ ትልቅ አቅም ይፈጥራልም ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com