“ሰንበት ለሰው እንጂ፥ ሰው ለሰንበት አልተሠራም!”

Views: 190

መንግሥት ሕግ ወይም መመሪያ የማውጣት ተመክሮው ለማሠራት ሳይሆን ለማሰር፤ ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ እንደነበር የሚተቹት ቤተልሔም ነጋሽ፥ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የወጣውንና በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነውን የኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት (የኤታስ) አገልግሎት አሰጣጥ ለመወሰን የወጣ ረቂቅ መመሪያን የመጣጥፋቸው ማጠንጠኛ አድርገዋል። መመሪያው ለዜጎች ደኅንነት ነው የወጣው የሚለውን መከራከሪያ ከመንግሥት አንጻር ወይስ ከተጠቃሚ አንጻር ነው በሚል ጠይቀው፣ እውነት ለደኅንነት የቆመውን ሁሉ የሚደግፍ አሠራር ይምጣ ሲሉ ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን የመልካም ወጣትን ዘመቻ ወይም ‘ኢኒሺየቲቭ’ መዝጊያ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው “ይበል”፣ “ይሁን” ብለው መመረቃቸውን፤ በዚያው ዕለትም በቅርቡ ከአንድ የጀርመን አገር ድርጅት የተሰጣቸውን 25 ሺሕ ዩሮ ለሥራው ማበርከታቸውን ተከትሎ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ባለሥልጣናትም የፕሮቴስታንት ክርስትና እምነት ተከታዮች ስለመሆናቸው የሚወጡ መረጃዎችንም በማመን፣ እንደ ሽሙጥና በመጽሐፍ ቅዱስኛ ለማናገር ከመሞከር የመጣ ነው ርዕሴ። ይህ ጽሑፍም ሆነ ይህቺ አጭር መግለጫ በምንም መልኩ የእምነቱን ተከታዮች እንደማንጓጠጥ ተደርጎ እንዳይወሰድ አሳስባለሁ። ይልቁንም ሐሳቤን በአግባቡ ያስረዳልኛል ብዬ በማመንም ነው ጥቅሱንና ሐሳቡን እንደ ርዕስና መነሻ መውሰዴ።

ይህን ካልኩ በኋላ፤
የአዲስ ዓመት ምኞት ወይም ዕቅድ ዝርዝር አውጪ አይደለሁም። ሕይወት በዘፈቀደ ይሆናል የምል አልያም “የዛሬ አምስት ዓመት ራስሽን የት ታይዋለሽ?” ለሚል የሥራ ላይ ቃለ መጠይቅ ጥያቄ “እስቲ መጀመሪያ ዓርብ ልድረስ” የምል ዓይነትም አይደለሁም። የማወቅ ዕድሉን ካገኘሁበት ጊዜ አንስቶ ለዓመት አይደለም ለዓመታት ለሳምንታትና ለወራት ሲያስፈልግና ከሥራ ጋር በተገናኘ ለቀናትም ጭምር በተጠና እንቅስቃሴ የምራመድ እንጂ። በከንቱ አልፈዋል ብዬ ከማስባቸው ቀደምት የጉብዝና ወራቴ ቁጭት ለማካካስ ብዙ የሔድኩ ነኝ ብዬ ማመኔም የዚሁ ውጤት ነው። ግን በአዲስ ዓመት ለዚህች ጋዜጣ ተከታታዮችና በዚህች ዓምድ በኩልም እንደኔ ላሉ ዜጎች፣ ለኢትዮጵያውያን አንድ ምኞት ቢኖረኝ ብዬ ሳስብ፣ የሚወጡ ሕጎች ሁሉ ለሰው ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ በዚህም ዜጎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ፣ አገራችንም በዚህ ምክንያት የተሻለ ደረጃ እንድትደርስ የሚያደርጉ ቢሆኑ ብዬ አሰብኩ።

ይሔ ሁሉ ዝብዝብ ከሌላ ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ ሊሠራ የታሰበ ሕግ/መመሪያ ረቂቅ መነሻነት እስቲ ሕግ ስታወጡብን ሰንበት ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት አልተሠራም የሚለውን አስቡ ለማለት ነው።

ስለ ሕጉ ከማንሳቴ በፊት ስለማሠራት ሳይሆን ስለማሰር፤ ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ ስለሚወጡ ሕጎች ግንዛቤ ማግኘት ከጀመርኩበት ክስተት ልነሳ። ቀደም ባለው የሥራ ዘመኔ በጋዜጠኝነት መስክ ሳለሁ ከመጀመሪያ ሥራዬ የአማራ መገናኛ ብዙኀን ቆይታ ቀጥሎ ሪፖርተር ጋዜጣና አሳታሚው ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ዋነኛ ቀጣሪዎቼ ነበሩ። ሪፖርተር ጋዜጣ በመንግሥት አሠራርና ፖሊሲዎች ላይ የሠላ ትችት በመሰንዘር፣ በተለይ በቀዳሚዎቹ ወራት በመንግሥት ሳይቀር የሚተገበር አቅጣጫና የመፍትሔ አቅጣጫ አመላካች የነበረበት ዘመንም ነበር። በዚህ የጋዜጣው የስኬት ወቅት ግን መረጃ የሚያገኝባቸው መንገዶችና ይፋ የሚያደርግበት አኳኋን የሚያስከፋቸው፣ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ጥርስ የነከሱ ወገኖችም ነበሩ።

በኋላ እነኝህ ወገኖች አየሉ፣ መንግሥትም ቆዳው እየሳሳ መጣና ሰውን (በተለይ በአሳታሚውና በወቅቱ እዚያ በምንሠራ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች እምነት ሪፖርተር ጋዜጣን) ማለትም ጋዜጦችን ለይቶ የሚመታ የሚሠራ ሳይሆን የሚያስር ሕግ ረቂቅ ይፋ ሆነ። በወቅቱ የነበረውን ተቃውሞና ጩኸት፣ በዚያን ጊዜ በቁጥርም በአቋምም ጥሩ የነበሩት የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት በሚያዘጋጇቸው ውይይቶች ላይ የነበረውን ሙግት የተሳተፈ፣ የሚዲያ ዘገባዎችን ያደመጠ የሚያስታውሰው ነው። ከሁሉ በላይ “የፕሬስ ነፃነትን ከስቅላት አድኑ” የሚለው የጋዜጠኝነትን ሥራ ለቅቄ ከሔድኩ በኋላ ሳይቀር በሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገፅ የሚወጣ የተቃውሞ ምልክትን የሚያሳይ፣ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የተዘጋጀ አርማ (ሎጎ) አይረሳም።

እንዳለመታደል ሆኖ ያ “የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ” ፀድቆ ሕግ ሆኖ ወጥቶ በቅርቡ ፀድቆ ይተካዋል ተብሎ እስከሚታሰበው እስካሁኑ ረቂቅ ዘመን ድረስ ሥራ ላይ ነበር። ብዙ የሚዲያ ተቋማት በዚያ ሕግ ምክንያት ከኅትመት ውጪ ሆነዋል። ብዙ ጋዜጠኝነትን ሙያ አድርገው ተሠማርተው የነበሩ ዜጎች ሌላ መስክ ውስጥ ለመግባት ተገደዋል። የሚዲያ ዕድገትም ባለበት ሒድ ሆኖ ቆይቷል። ምናልባትም የለውጥ ተስፋ መጥቶ አዲስ ማለዳን ጨምሮ ብዙዎች አዲስ የኅትመትና የኤሌክትሮኒከ መገናኛ ብዙኀንን እንዳዲስ እስካገኘንበት እስካለፈው አንድ ዓመት ገደማ ድረስ።

ከዚያ ብዙ ዝነኝነታቸው ለክፉ የሆነ፣ ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ የወጡ ሕጎች መጡብን። ብዙዎችን ያለ በቂ ምክንያት ወህኒ ለማውረድ መሣሪያ የሆነው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ፣ በርካታ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንና ለዜጎች ይሠሩ የነበሩ ማኅበራትን ለቀብር የዳረገው አሣሪ ብቻ ሳይሆን ገዳይ ሕግ – የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ወዘተ ከመመሪያና ሰርኩላር እስከ በማሻሻያ ሥም የሚወጡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን መብቶች በጓሮ የሚወስዱ ምርጫ የሚያሳጡ (እንደ መጀመሪያ በፈቃድ ከዚያ በግዴታ የመጣው የግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስትና) አሠራሮች በረከቱ። ከቋንቋ ፖሊሲው እስከ የትምህርት ፖሊሲው መንግሥት በይፋ ጥፋት እንደሠራ ብቻ ሳይሆን ትውልድ ገዳይ ተብለው የሚቀርብባቸው ወቀሳ እውነት መሆኑን እስኪያምን ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ፣ የሚያመጡት ጉዳት እየታየና እየተገለጸም እንኳን በ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” እና ተራ ብሽሽቅ በሚመስል መልኩ በግዴለሽነት ለዓመታት የአሠራር መመሪያ ሆነው ከረሙ።

ከላይ የጠቀስኳቸውና በክፋት ዝና የበዛላቸው ሕጎች የተወሰኑት ተሻሽለዋል፤ ይህም ተስፋ የሚሰጥ ነው። ነገር ግን ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሑፎች እንዳየሁት እንደ የምርጫ ቦርድ አዲስ አዋጅና የጎዳና ላይ ልመናንና ሴተኛ አዳሪነትን እንደሚከለክለው ያለ ሕግ በተለይ የሴቶችን መብቶች አሳንሶ የማየትና የመሸርሸር የተሰጠውን ለመውሰድ ያለመ በሰው ላይም ባይሆን ለሰው ቁብ የማይሰጥ የሚመስል ሕግ ሲወጣ እያየን ነው። በተለይ መንግሥት “መንግሥትና ሃይማኖት ለየቅል ነው” ከሚለው ወይም “መንግሥት ዓለማዊ ነው/ሃይማኖት የለውም” መርህ የወጣ መስሎ የሞራል አስተማሪ ሊሆን እየተንደረደረ በሚመስልበት በዚህ ወቅት ለሰው ሳይሆን በሰው ላይ የሚወጣ ነገር አለመኖሩን ብንጠራጠር አይፈረድብንም።

ይሔ ይህን ሁሉ ለማለት ወዳነሳሳኝ አዲስ የሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነ ሕግ ይወስደናል።
ባለፈው ሳምንት በአንዱ ቀን ጠዋት እንደልማዴ ማኅበራዊ ሚዲያውን ስቃኝ ትዊተር ላይ ራይድ ብለን የምንጠራውን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመውን ሃይብሪድ ቴክኖሎጂስ የተሰኘ ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ያጋራችውን መልዕክት ሰው “ከራይድ ጎን ነኝ” እያለ ይመለከታቸዋል የሚለውን የመንግሥት ባለሥልጣናት የትዊተር አድራሻ እየጨመረ በስፋት ያጋራው ይዟል። ራሴም ከመልዕክት ጋር ወዲያውኑ ያጋራሁት በእንግሊዝኛ የተፃፈውና ወደ አማርኛ የመለስኩት የሥራ አስኪያጇ መልዕክት እንዲህ ይላል።

“እንዲህ ኢትዮጵያዬ የገጠሙንን ተግዳሮቶች ሁሉ ለማለፍ ጠንክሬ እየሠራሁ ነው። አገሬ ስለሆነ ከዚህ የትም አልሔድም ”
በኋላ ሰዎች በዚሁና በሌላውም ማኅበራዊ ሚዲያ ካጋሯቸው መረጃዎች ለመረዳት እንደቻልኩት የአዲስ አበባ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ራይድ እና ሌሎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ የታክሲ ማኅበራትን የሚገዛ አዲስ ረቂቅ አውጥቷል። ከዚህ በፊት ምናልባትም በዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር እንደታየው ራይድ አገልግሎቱን ለማስቆም እስኪደርስ የዘለቀ በቢሮው የመጣ “እናንተ የምትገዙበት መመሪያ የለኝም። ስለዚህ መሥራት አትችሉም” የሚል መግለጫ (ይታያችሁ እነሱ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አሠራር ላይ ቆመው ይህ በጎረቤት ኬንያ ሳይቀር ከዜጋ እስከ ጎብኚ እፎይታ ያመጣ ቴክኖሎጂ ወደ አገራችን እንደሚመጣ አስበው ቀድመው ሳይዘጋጁ መቆየታቸው ሳያንስ) እንካሰላንቲያ ተፈጥሮ ዜጎችም ተቃውመው መመሪያ እስክናዘጋጅ ሥሩ ተብሎ እስኪፈቀድ ብዙ ግርግር ነበር። ሕጉ ሲመጣ ግን ሌላ አስገዳጅ የሚያሠራ ሳይሆን የሚከለክል ሆኖ መጣ።

ረቂቁ ቀለም ቀብተው ይህንን ሥራ ብቻ እንዲሠሩ ከሚል የደንበኞቹን እንቅስቃሴ በሙሉ መረጃ መስጠትን አስገዳጅ እስከሚያደርግ አንቀጽ ድረስ ይህን ለዜጎች፣ በተለይ ለሴቶች ደኅንነት አመቺ የሆነ፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው ተመጣጣኝ ዋጋ የሚያስከፍል አሠራር በሙሉ ለማጥፋት የተነሳ የሚመስል ሕግ መጥቷል እየተባለ ነው። ጥቂት ከሚባሉ ድጋፍ መሠል ክርክሮች በቀር በአብዛኛው ከራይድ ጎን የቆሙ አስተያየቶችና ሐሳቦችን እያየን ነው። በዚህ የተበረታታ የሚመስለው ድርጅትም ከምስጋና መልዕክት አልፎ አሁንም ሥራችንን በአግባቡ እየሠራን ነው ስለድጋፋችሁ እናመሰግናለን የሚል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ለደንበኞቹ በተንቀሳቃሽ ስልካችን እስከ መላክ ደርሷል።

በበኩሌ ባለፉት ዓመታት የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚም ባልሆን በጎበኘሁባቸው ከተሞች ከናይሮቢ እስከ ካምፓላና ፕሪቶሪያ ኡበር የተሰኘው ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ በሚሰጠው ፍፁም ደኅንነቱ የተጠበቀ በማያውቁት አገር ከመደናበርና ለደኅንነት ከመስጋት እንዲሁም አለአግባብ ገንዘብ ከመበላት ያዳነ ቴክኖሎጂ አዲስ አበባስ ወጓ መች ይሆን ያሰኘን ነበር። ራይድ ሲመጣ ከተደሰቱት ውጪ አገር ጉዞ ማድረግን ጨምሮ የቢሮ ተሸከርካሪ በማይኖርበት ለሥራ ለመንቀሳቀስ ከመጠቀም የራይድ ደንበኛ፣ በአገልግሎቱ የሚከፈለው እጅግ ተመጣጣኝ ዋጋም አመስጋኝ ነበርኩ።

ታዲያ “ይህቺም እንጀራ ሆና ሻጋታ በዛባት” እንደሚል ዕድለ ቢስ ይህቺን ትንሽ ተስፋ ለማጨለም፣ በተለይ በማታ በሥራ ምክንያት የመንቀሳቀስ ግዴታ ላለባቸው ሴቶች እፎይታ የሰጠ የደኅንነት ሥጋትን ያስቀረን ፈጠራ ለማስቆም የተነሰን ሐሳብ “ሰንበት ለሰው እንጂ፥ ሰው ለሰንበት አልተሠራም” ብንለው ይፈረድብናል?
ተስፋችን በከንቲባው ትዊተር ምላሽ “ለዜጎች ደኅንነት ስንል ነው ያወጣነው” የተባለ ነገር ከእነሱ (ከመንግሥት) ሳይሆን ከእኛ (ከተጠቃሚ) አንጻር የእውነት ለደኅንነት የቆመውን ሁሉ የሚደግፍ አሠራር እንዲመጣ ነው!

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com