መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ?

Views: 574

ካሳዬ አማረ ፅንፍ የረገጡ የጎሣ ብሔርተኞች ዓላማና እንቅስቃሴ ውስጡ ሲፈተሸ ምን እንደሚመስል እንዲሁም ያስቀመጡትነም ግብ ለመምታት እንዲረዳቸው የሚጓዙበት መስመር አገር ላይ አደጋ የሚጋብዝ ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት ሁኔታ የመንግሥት ዝምታ ማለት ለምንድን ነው ሲሉ ይጠይቃሉ፤ የቢሆን ግምታቸውንም ዘርዝረዋል። ለዘላቄታው በአገር አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ የጎሣ ብሔርተኝነት እና የዜግነት ብሔረተኝነትን የሚያስተናግድ ስርዓት መፈለጉ ይታሰብበት ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

የጎሣ ብሔረተኞች መስመር
ብዙዎቹ የአፍሪካ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ከሚያቀርቡት ሚዛናዊ ሐሳብ አንዱ ስለ ጎሰኝነት ነው። በአፍሪካ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጎሰኝነት የሰላም እና የልማት ኀይል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ያስገነዝባሉ። አክለውም በአፍሪካ ደረጃ መልከዓ ምድራዊ ጎሣ (Geo-ethnic) በመባል የሚታወቁት እና በተወሰነ ሥፍራ ላይ ሰፍረው የሚገኙት መልከዓ ምድራዊ ጎሣዎች አገራዊ ልማቱን ለማፋጠን የሚሠሩ እና ግጭት አልባ ግንኙነቶችን በማሳደግ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱ የአንድነት ኀይሎች መሆናቸውን ያስረዳሉ። ወደእኛ አገር ስናመጣው እነዚህን ኀይሎች በአግባቡ ባለመጠቀም ሕዝቡ ኑሮ ከምችለው በላይ ሆነብኝ፣ የምግብ ያለህ ይላል የጎሣ ብሔርተኞች ግን ንትርክን፣ መለያየትን አልፎም ግጭትን በየዓይነቱ ያቀርቡለታል።

የፅንፍ ጎሣ ፖለቲካ ዙሩ ከሮ አቀንቃኞቹ መሠረታዊ እና የጋራ ችግሮቻችን ላይ ከማተኮር ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፉ አጀንዳዎችን በማራገብ ተጠምደዋል። በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ወይም ‘ጠላታችን’ ነው ካሉት አካል ወይም ቡድን መረጃ ሲወጣ ያንን ተንተርሶ ሌላ ትርክት ማሰራጨት፣ በመንግሥት አካላት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የሐሳባቸው ተከታይ ማድረግ የመሳሰሉት እየተፈፀሙ ነው።

ሐሳብን በነፃነት መግለጽ መብት ነው። መብት ምን ጊዜም ከግዴታ ተለይቶ የሚታሰብ ባለመሆኑ በምንጠቀመው መብት መሠረት የምናቀርበው ሐሳብ ውስጥ ግዴታ ያለ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ከፅንፈኛ የጎሣ ብሔረተኞች እየቀረቡ ያሉ ሐሳቦች ለምን ተነሱ አይደለም ግን ግዴታ የጎደላቸው አገርን ለትርምስ የሚጋብዝ መሆኑ ትኩረት የሚያሻው ሆኗል።

ለምሣሌ አንዱ ሲቀርብ የነበረው ተረት አፄ ምኒልክን ‘አላውቃቸውም’። ለመሆኑ አላውቃቸውም ማለት ስለመኖራቸው በንባብ፣ በትምህርት አላገኘሁትም ማለት ነው ወይስ አላውቃቸውም በማለት የማሳነስ ዘዴ ነው። ይህ ሐሳብ ሰላማዊ ክርክር ለማድረግ የማይጋብዝ የአስተሳሰብ ድንክነት ነው። እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን ወራሪው አገር ጣሊያን እና መሰል የውጭ መንግሥታት በሰፊው የፃፉላቸው ናቸው። በጋራ እሳቸውን የሚገልጿቸው “ምኒልክ ጥበበኛ የፖሊቲካ ሰው እንደሆኑ ነው”። አፄ ምኒልክ ለአገር ጎጂ መሪ ሳይሆኑ ከዘመኑ የቀደሙ እና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት ሆነው ያለፉ ናቸው። ባለሥልጣኖቻቸውን ወደ ቤተመንግሥት ያስገቧቸው ዘርን መሠረት አድርገው ሳይሆን ለአገር የሚበጅ ሥራ ይሠራሉ ብለው ያመኑባቸውን ነው።

በሌላ ጎኑ ደግሞ በትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ ስለአማርኛ ቋንቋ የቀረበው ሐሳብ በተገኘው አጋጣሚ ለአሰቡት ድብቅ አጅንዳ ሕዝብ ማሰባሰቢያ እንዲሆን ሐሳቡን ገበያ ላይ ማውጣት ስለነበር የሚዲያዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። በመጀመሪያ ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ላይ አማርኛ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጣል የሚል በሌላ ጎን ደግሞ ከ3ተኛ ይጀምራል የሚል የተምታቱ ሐሳቦች ነበሩ። ግባችን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ማደግ፣ መበልፀግ ከሆነ ሕፃናት ተጨማሪ ቋንቋ ማወቃቸው ይጠቅማቸዋል እንጂ የሚጎዳቸው እንዳልሆነ የቋንቋ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። አገራት ቋንቋቸው እንዲታወቅ፣ እንዲነገር ማዕከላት በማዘጋጀት ያስተምራሉ። በእኛዎቹ የጎሣ ብሔረተኞች ግን ቋንቋን ለማራራቂያ መሣሪያነት ለመጠቀም ሌት ተቀን ይባክናሉ። በዚሁ አጋጣሚ ትምህርት ሚኒስቴር በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየሠራ ነው ወይስ ሥልጣኑን ለክልሎች አሳልፎ እየሰጠ ነው ወይ የሚለው ወደ ፊት ሊታይ የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ነው።

ስለ ቋንቋ ከቀረበው ጋር አብሮ የሚሔደው እና ከላይ የቀረበውን ሐሳብ የሚያጠናክረው የግል ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ከሚዲያዎች ተከታትለናል፣ በዚህም ብዙ ሕፃናት የመማር እክል ይገጠማቸዋል። ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርታቸውን የመከታተል መብት አላቸው። በተጨማሪ የአካባቢውን ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መማራቸው ለልጆቹ የሚጠቅም ስለሆነ የሚያከራክር አይደለም። ትክክል ያልሆነው ለሕፃናት ተማሪዎቹ የትምህርት ቋንቋ መምረጡ የወላጆቻቸው ኀላፊነት ሆኖ ሳለ ትምህርት ቤቶቹን ሙሉ በመሉ መዝጋት የሕፃናቱን የመማር መብት የሚደፈጥጥ ነው።

በሌላ ጎን ደግሞ ሃይማኖትን መሣሪያ ማድረግ ሌላው የፅንፈኛ ብሔረተኞች ትኩረት ከሆነ ሰነባበተ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማትከፋፈል በአንድ የአደረጃጀት ስርዓት የተዋቀረች ጥንታዊ የእምነት ተቋም ነች። ሆኖም በውስጧ የበቀሉ አረሞች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመነጠል የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለመመሥረት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ከሚዲያ ሰምተናል። በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ምዕመናን ማግኘት የሚገባቸውን የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በቋንቋቸው የሚሰብኩ ካህናትን በማፍራት በኩልና እና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችን በተመለከተ መጠየቃቸው አግባብነት አለው። ይህንን መሠረት በማድረግም ድጋፍ በመስጠት እና ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው መፍትሔ በማመላከት በኩል የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ አጋጣሚውን ለጠባብ ፍላጎት ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ተቀባይነት የለውም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ አንድነት ዋልታ እና ማገር መሆኗ ማንም የማይክደው ነው። ስለሆነም ይህችን አንጋፋ እና ጥንታዊት ቤተክርስቲያን በማዳከም እና አገር በማተራመስ ለ‘አገር’ ምስረታ ህልማቸው ወይም የራሳቸውን ፍላጎት በብዙኀኑ ላይ የመጫን አዝማሚያ ለአገርም ለሕዝብም የሚያዋጣ መስመር አይደለም።

የመንግሥት ዝምታ፣ ለምን?
በሠላም፣ በፍቅር በመደመር ወደ ጋራ ብልፅግና ማምራት ይቻላል በሚል ከግራ እና ከቀኝ የሚቀርቡ ሐሳቦች በነፃነት ይንሸራሸሩ፣ በመጨረሻ የሚጠቅመው እና የማይጠቅመውን በመለየት ወደ ጋራ መግባባት መምጣት ይቻላል የሚለው መንገድ መልካምነት አሌ የሚባል አይደለም። ሆኖም አቧራ የሚያስነሱ ጉዳዮች በሚራገቡበት፣ ወደ ግጭት የሚያንደረድሩ ሐሳቦች በሚናኙበት እና በሕዝቡ ላይ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ እየመጣ ባለበት፣ ከኹለት መጥፎ ምርጫዎች አነስ ያለው መጥፎ ይሻለናል የሚሉ ሐሳቦች በሚቀርቡበት ወቅት መንግሥት ለምን ዝም ይላል? በግሌ ለዝምታው መነሻ ናቸው ብዬ ያመንኩበትን ‘ይሆናሎች’ እንደሚከተለው አቅርባለሁ። እነዚህም፡-
(1) ፅንፈኛ የጎሣ ብሔረተኞቹ ላይ መንግሥት እርምጃ ቢወሰድ የሚያንቀሳቅሱት ወይም ያላቸው ተከታይ ብዛት ምክንያት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት አይቶ እንዳላየ የመሆን ስልት መከተል፣

(2) ሕዝቡ በጨቋኝ ገዢዎች እና አስተዳደር ሥር በመውደቁ ምክንያት ለብዙ ዘመናት ሐሳቡን በነፃነት መግለፅ ያልቻለ በመሆኑ አሁን መብቱ ገደብየለሽ ሲሆን የሚቀርቡ ሐሳቦች ግርታ ሊፈጥሩ መቻላቸው፣ ከጊዜ በኋላ ትዕግሥት በተላበስ መስመር ሲያዙ የሰከኑ ሐሳቦች ስለሚመጡ በአገር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያስከትልም የሚል ሙግትን መሠረት በማድረግ መንግሥት ሐሳቦች በነፃነት እንዲሸራሸሩ በመፈለግ ጣልቃ መግባት አለመፈለጉ፣

(3) ኢሕአዴግን በመሠረቱት አራቱ ግንባሮች ውስጥ ያለው ፍትጊያ እና የኀይል አሰላለፍ መዋዠቅ ያስከተለው ተፅዕኖ እና ግፊት ናቸው። በተለይ በመቀሌ የሚካሔዱ ስብሰባዎች፣ የአቋም መግለጫ ማውጣት የኀይል አሰላለፉን በመቀያየር በፌደራል መንግሥቱ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር እና ግንባሩን የመሰንጠቅ፣ የማግለል እንቅስቃሴ መታየት ናቸው።

ለእኔ ኹለተኛው እና ሦስተኛው ነጥቦች ገፊ ምክንያት ናቸው ብዬ አምናለሁ። ለዝምታው ሌላ ምክንያት አለን? ወይስ መንግሥት ዝም አላልኩም ብሎ ይሞግታል።
በአገራችን ውስጥ ከሚያስገርሙን የፖለቲካ ጉዳዮች መካከል አንዱ ብዕር ይዘው የሚከራከሩ፣ በሰላማዊ መንገድ ለአገር ይጠቅማል የሚሉ ሐሳቦችን የሚሰነዝሩ ዜጎች እና በዓላማ የተሰባሰቡ ቡድኖችን ማዋክብ፣ ማሰር፣ በፀረ ሽብር አዋጅ ክስ መመሥረት በአንድ ጎን፣ በሌላ ጎን ደግሞ በአደባባይ ሕዝብን የሚያተራምስ ቅስቀሳ እና የጥላቻ ንግግር/መልዕክት በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች መንገዶች የሚያቀርቡ ግለሰቦች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ማየት አጀብ የሚያሰኝ ነው። በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ነው የሚለው ነባር መርህ የተዘነጋ ይመስላል። የጆርጅ ኦርዌልን “ሁሉም እንሰሳት እኩል ናቸው ጥቂቶቹ ግን የበለጠ እኩል ናቸው” የሚለውን ሐሳብ ያስታውሰናል። ስለዚህ በመንግሥት በኩል መንግሥታዊ ኀላፊነት ሳይሸራረፍ እና ሳይዛነፍ ተግባራዊ መደረግ አለበት።

ሌላው አስደናቂው ጉዳይ በባለሥልጣን በኩል የወጣ የመንግሥት መግለጫ በማግሥቱ መግለጫው እንደተቀለበሰ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘግቡት መሆኑ እና በትክክልም እንደተቀለበሰ ሲታወቅ መንግሥት ማነው እንድንል የሚገፋፋ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። ግለሰቦች የሚዘውሩት መንግሥታዊ አካል አለን፣ አገሪቱን ወይም ክልሉን እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ እየመሩ ነውን ከማለታችን በተጨማሪ መንግሥት በሕዝብ ውስጥ ያለውን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።

የማንኛውም መንግሥት አንዱ ኀላፊነት የሕዝቡን ሠላም እና ደኅነንት መጠበቅ እና ማስከበር ነው። ሰላም ሲባል የጥይት አረር የማይጮህበት ብቻ አይደለም ሕዝቡ የአእምሮ ሰላም አግኝቶ የተረጋጋ ሕይወት እንዲገፋ ማድረግን ያጠቃልላል። በሌሎች አገራት ያሉ መንግሥታት ልምድ እንደሚያሳየን መሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ አገር ዐቀፍ መግለጫ ቢሰጡ መልካም ነው። እንደ አማራጭ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት በኩል ለሕዝቡ መግለጫ መስጠት፣ ወቅታዊ መረጃ ለሕዝቡ እንዲደርስ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። የመሪዎች ወይም የፕሬስ ሴክሬታሪያት መግለጫ በኅብረተሰቡ ውስጥ መረጋጋት ይፈጠራል፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን መለየት ያስችላል፣ በተሰጠው መረጃ መሠረት አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ያስችላል። በዚህም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ይቻላል፣ በመቀራረባቸው ይደጋገፋሉ፣ መናበብም ይችላሉ።

በመጨረሻ ለዘላቂ መፍትሔ በአገር አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ የጎሣ ብሔርተኝነት እና የዜግነት ብሔረተኝነትን የሚያስተናግድ ስርዓት መፈለጉ ላይ ሊታሰብበት ግድ ነው። ሁሉንም ኀይሎች የልማት መሣሪያ በማድረግ፣ ያለብንን ብሔራዊ ፈተና፣ ድኅነትን በመቀነስና በማጥፋት እና ብሔራዊ ሀብት በመፍጠር በኩል በሚደረግ እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ የኹሉቱንም ኀይሎች አስተሳሰብ የሚያራምደውንና ከኹሉቱም ውጭ የሆነውን ሕዝብ በማንቀሳቀስ፣ በማሳተፍ ችግሮቻችንን መፍታት ያስፈልገናል። አስከትሎም ደረጃ በደረጃ በጎሣ እና በዜግነት ብሔረተኝነት ምትክ የገበያ ብሔረተኝነት (Market Nationalism) ደረጃ በደረጃ እንዲያቆጠቁጥ በማድረግ የሕዝቡን ሰላም እና የአገር አንድነትን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እና ብልፅግናን እውን ማድረግ ይቻላል።

ካሳዬ አማረ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። በኢሜል አድራሻቸው amarek334@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com