በመንግሥት ትኩረት መነፈግ ዋጋ እየከፈለ ያለው አካል ጉዳተኝነት

Views: 457

በብሔራዊ ዐይነ ሥውራን ማኅበር ሥር በሚተዳደረው የወላይታ ዐይነ ሥውራን ትምህርት ቤት በማኅበሩ ድጋፍ ትምህርቱን ተከታትሎ፣ በዘንድሮ ዓመትም በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በመምህራን ማሠልጠኛ ፕሮግራም በዲፕሎማ የተመርቀው ዐይነ ሥውሩ ድረስ ሁናቸው፣ ከሌሎች ተመራቂዎች ጋር ሥልጠና ወስዶ የሥራ ቦታ ለመመደብ ዕጣ የወጣለት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመሆኑ፣ ከሚኖርበት አቃቂ ክፍለ ከተማ ስለሚርቅ ወደተመደበበት ክፍለ ከተማ ሔዶ እንዲቀይሩት ጥያቄ ያቀርባል።

እዚያም አቃቂ ክፍለ ከተማን እንዲጠይቅ ስለተነገረው፣ ጥያቄውን ለማቅረብ ወዳቀናበት አቃቂ ክፍለ ከተማ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ 7ኛ ፎቅ ደርሶ ወደ ታች ለመውረድ የአሳንሰሩን ቁልፍ ይጫነዋል። ተከፈተለት። አሳንሰሩ ግን ወለል አልነበረውም፤ 21 ሜትር በሚገመተው የአሳንሰር ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ሕይወቱ አለፈ።
ድረስ ላይ የደረሰው የሕይወት መቀጠፍ አሰቃቂው ሆነ እንጂ ሌሎች አካል ጉዳተኞች ላይም ካለመመቸት እስከ አካል ጉዳት በተለያየ መሰረተ ልማት ምክንያት መድረሳቸው እንግዳ ደራሽ አይደለም።

ይህም መንግሥት ለኣካል ጉዳተኞች እየሰጠ ያለው ትኩረት አናሳ ስለመሆኑ ማሳያ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ናቸው። በወቅቱ ለተከሰተው የሞት አደጋ መንስኤው በሚኖርበት አካባቢ እና የተመደበበት የሥራ ቦታ ርቀት ያላቸው በመሆኑ ለማስቀየር በሔደበት ወቅት ነው ብለዋል። “መንግሥት ለኣካል ጉዳተኞች ሕይወት ግድ የለውም፤ በተደጋጋሚ በከተማዋ ውስጥ በመንገዶች ተሟልቶ አለመገንባት እና የሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን ተከትሎ፣ በተደጋጋሚ ለአደጋ እየተጋለጡ ይገኛሉ። በሊፍት አደጋ ሕይወቱ ያለፈው ድረስ ሁናቸውም ጉዳይ ለዚህ ማሳያ ነው” ሲሉ ትኩረት መነፈጋቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከክስተቱ በኋላም ፌዴሬሽኑ፣ መንግሥትን የመጠየቅ፣ የማሳመን፣ የማስገደድ፣ ብሎም የመክሰስ ኀላፊነቱን ለመወጣት ከሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመለከታቸው ኀላፊዎች ጋር በአካል ጉዳተኞች የሥራ አመዳደብ ጉዳዮች ላይ መወያየታችውን ይገልፃሉ።

እንደ አባይነህ ገለፃ፣ ኮንስትራክሽን ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ወደጎን የተወ ተቋም ነው። መንገዶች፣ ውሃ መውረጃዎች፣ በተለይም ግንባታቸው ባልተጠናቀቀ ሕንፃዎች ምድር ቤቶች አገልግሎት እንዲሰጡ መፈቀዱ፤ አገልገሎቶቹ አካል ጉዳተኛውን ያላገናዘቡ እና የሚያገሉ መሆናቸውን ያነሳሉ። የአዲስ አበባ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ እፈጥራለሁ ቢልም አፈጻጸም ላይ ግን ደካማ ነው ብለዋል። አያይዘውም፣ መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደ ዕርዳታ አድርጎ መቁጠር የለበትም፤ የመብት ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለበት ብለዋል።
የትነበርሽ ንጉሴ (ሎሬት) በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዳሉት፣ ለዚህ ዋና ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። በትልልቅ የፖሊሲ መድረኮች የአካል ጉዳተኛው ችግር በበቂ አይነሳም። ይህም ከሥር ጀምሮ ያሉ ችግሮች መፍትሔ እንዳያገኙ አድርጓል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ መድረኮች የኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ የንግድ ማዕከላት፣ መንገዶች ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለአካል ጉዳተኛው ምቹ እንዳልሆኑ ተነስቷል። ሆኖም ችግሩ አዲስ በሚሠሩ ግንባታዎች ላይ ሲቀረፍ አይታይም። አንዳንድ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኛ መወጣጫ ቢኖራቸውም፣ ከፍታ ያላቸው በመሆኑ ለዊልቸር ተጠቃሚዎች አመቺ አይደሉም። ሊፍቶችም ቢሆኑ ብዙ ቦታ አንድ ዘሎ አንድ ናቸው፤ የማይሠሩም አሉ። የሕንፃ አዋጁ ሕንፃዎች ሲገነቡ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ ዲዛይን እንዲኖራቸው ቢያስቀምጥም፣ ይህ ብዙም ሲተገበር አይታይም ሲሉ ገልጸዋል።

በየመንገዱ የተቆፈሩ ጉድጓዶችና ሌሎችም ተምሮና ወጣ ብሎ ራሱን ለመቻል የሚለፋውን አካል ጉዳተኛ እየፈተኑት ነው ያሉት አባይነህ በበኩላቸው፣ በመንግሥት የሚገነቡ ሕንፃዎችም አካል ጉዳተኛውን በቅጡ ያገናዘቡ አይደሉም ይላሉ። የሕንፃ አዋጁን በመጀመርያ የጣሰው መንግሥት መሆኑን የሚያወሱት አባይነህ፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚሔድ አካል ጉዳተኛ ተደራሽ የሆነ ግንባታ ባለመኖሩ እንደሚቸገር በመግለጽ፣ ሕይወቱን በሊፍት ያጣውን ወጣት በምሳሌነት ያቀርባሉ።

የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመጥቀስም ባለዕድሉ አካል ጉዳተኛው ከሆነ የወለል ክፍል እንደሚሰጥ፣ ሆኖም እናት/አባት ባለዕድለኛ ቢሆንና አካል ጉዳተኛው ልጁ ቢሆን፣ የወለል ክፍል እንደማያገኝ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ብዙ እናቶች ተከራይተው ለመኖር መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

አባይነህ በኢትዮጵያ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ግልጽ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ በወጣው መረጃ ከሕዝቡ 1.17 በመቶ ማለትም 1.17 ሚሊዮን አካል ጉዳተኛ አለ ማለቱንና፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም ባንክ በ2011 ያወጡት ሪፖርት 17.6 በመቶ ወይም 17.6 ሚሊዮን እንደሚል ጠቅሰው። ይህንን በተመለከተ በመጪው ዓመት የሚካሔደው ሕዝብ ቆጠራ ግልጽ መረጃ እንደሚሰጥ ተስፋ እንዳላቸው፣ አካል ጉዳተኞች በቅጡ ካልተቆጠሩ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ጥቅምት 10/2011 በኢትዮጵያ ናሽናል ዲስኤቢሊቲ አክሽን ኔትወርክ በተዘጋጀ መድረክም በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛው ቁጥር በግልጽ እንደማይታወቅ ተነግሯል። አካል ጉዳተኞች የተሻለ ትምህርት ያለማግኘታቸው፣ የሥራ ማስታወቂያዎች ተደራሽ አለመሆን፣ በቀጣሪ በኩል አዎንታዊ ምልከታ እንደሌለም ተገልጿል።
ትምህርቱ ለአካል ጉዳተኛ በበቂ ተደራሽ ባለመሆኑ ቤት የቀሩ፣ ከድኅነታቸው ብዛት በየእምነት ተቋማቱ ምፅዋት የሚጠይቁ አካል ጉዳተኞችም በርካታ ናቸው። እነዚህን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አገሪቷ አጀብ የተባሉ ፖሊሲዎች ቢኖሯትም አፈጻጸማቸው ላይ ያለው ክፍተት በመድረኩ የተነሳ አጀንዳ ነው።

የአካል ጉዳተኛ ሰዎች መብቶች ከሕግ አንጻር ሲዳሰስ
እንደ አባይነህ ገለጻ፣ በተለይ ከ1983 ወዲህ ብዙ ሕጎች ወጥተዋል። ሆኖም አፈጻጸም ላይ መንግሥት ዛሬም ወገቤን ይላል። በአካል ጉዳተኛ ዙሪያ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከፍተኛ ነው። በመከራ ደረጃ እየወጡ የተማሩ አካል ጉዳተኞች ሥራ አላገኙም፤ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቁጭ ያሉ አሉ። “ፖሊሲዎች አካል ጉዳተኛውን በሚደግፍ መልኩ ተቀምጠዋል። አስፈጻሚዎች የት አሉ? አስፈጻሚው የግድ አካል ጉዳተኛ መሆን አለበት? በከተማዋ ያሉት ሕንፃዎች ሁሉንም በእኩል አያስተናግዱም። አንድ ሕንፃ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገንብቶ ለአካል ጉዳተኛው ግን ተደራሽ አይደለም” ሲሉ አባይነህ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ከአካል ጉዳተኞች መብት ጋር በተያያዘ በወጣው የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ 624/2001 ስለ አካል ጉዳተኞች ግልጽ የሆነ ድንጋጌ ከያዙት መካከል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት የአዲስ አበባ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አስቻለው ደምሴ፣ አዋጁ በአንቀጽ 36 አካል ጉዳት ስላለባቸው ሰዎች የሚደረጉ ዝግጅቶችን በሚደነግገው አንቀጽ ሥር ማንኛውም የሕዝብ መገልገያ በሆኑ ሕንፃዎች ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር ለሚንቀሳቀሱ ወይም መራመድ ለሚችሉ፣ ነገር ግን ደረጃ መውጣት ለማይችሉ ሰዎች ለመንቀሳቀስ የሚመች መዳረሻ መዘጋጀት እንዳለበት ይደነግጋል ብሏል። የመጸዳጃ ቤት በሚሠራበት በማንኛውም የሕንፃው የውስጥ አካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች የሚመቹ እና ሊደርሱባቸው የሚችሉ በቂ መጠን ያላቸው መጸዳጃ ቤቶች መኖር እንዳለባቸውም አውጇል።

እንዳስቻለው ገለጻ፣ ይሁን እንጂ ሕንፃ ዲዛይን ከሚያደርጉ ሰዎች ጨምሮ የሕንፃ ባለቤቶችም ሕጉን ተግባራዊ ሲያደርጉ አይታዩም። ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የማስፈጸም አቅማቸው ዝቅተኛ ሆኖ ታይቷል።

አንድ ሕንፃ ሲገነባ ምን ማሟላት እንዳለበት በአዋጅ፣ በመመሪያ ተቀምጧል የሚሉት የትነበርሽ፣ በቅርቡ የተገነቡት እንኳን መመሪያውን እንደማያሟሉ ገልጸው፣ አካል ጉዳተኛውን ሊታደግ የሚችል መንግሥት የለም ወይ? እስኪባል አብዛኞቹ ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም። አንዳንዶቹ ለአካል ጉዳተኛ መረማመጃ ቢሠሩም ምቹ አድርገው አልሠሯቸውም። በጣም የተንጋለሉ ናቸው። የተሠሩ መወጣጫዎች (ራምፖች) ምቹ አይደሉም። አንዳንድ ቦታዎች እሥረኛ ሊፍቶች አሉ። አካል ጉዳተኛውን ብቻ ሳይሆን ነፍሰጡርና አረጋውያንን ጭምር ያስጨንቃሉ። አንዳንዶቹ ሊፍቶች ከኹለተኛ አንዳንዶቹ ከአራተኛ ፎቅ ይጀምራሉ። ጎዶሎ ቁጥር የማይሠሩባቸው አንድ ወደ ላይ ወይም አንድ ወደ ታች እንዲወርድ የሚያስገድዱም አሉ። እሥረኛ ሊፍቶች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በተለያዩ ተቋማትም አሉ። ሕጉ ከወጣ መከበር አለበት። ግን እየተከበረ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።

ሕጉ ራሱ ሕንፃ ዲዛይን የሚያደርጉ ሰዎች አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ እንዲያደርጉ ያዛል የሚሉት አባይነህ፣ ለአካል ጉዳተኛ የሚያስፈልግ መፀዳጃ፣ ሊፍት ውስጥ ለዓይነ ስውራን የሚሆን ብሬልና ሌሎችም መሟላት ያለባቸውን ሁሉ አንድ ሕንፃ እንዲያሟላ በሕጉ መቀመጡን ይናገራሉ። በእኛ በኩል አቅም ያላቸውንና ጨረታ ተወዳድረው ሊያሸንፉ ይችላሉ ያልናቸውን አርክቴክቶች ጠርተን በአዲስ አበባና በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ውይይት አካሒደናል። በእነሱ በኩል የተነሳው ጉዳይ የሕንፃው ባለቤት እንደፈለገ የሚያዝ በመሆኑ ሕጉን ለመተግበር አለመቻሉን ነው። ሆኖም ችግሩ ከሕንፃ አስገንቢዎችም ቢሆንም አርክቴክቶች ባለሀብቶችን ስለሕጉ መምከር አለባቸው። አገልግሎት መስጫ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ፣ መኖሪያ ቤቶችም አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ አድርገው መሠራት አለባቸው። የአቅም ችግርና ተጨማሪ ወጪ የሚሉት ጉዳይ ቢኖርም፣ አካል ጉዳተኛውም ተጨማሪ አገልግሎት ፈላጊ ይሆናል። አካል ጉዳተኛው ገንዘቡን ባንክ አስቀምጦ የማያወጣበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ብዙዎቹ በደረጃ የሚወጡ ናቸው። ዓይነ ስውራን ገንዘባቸውን ባንክ ማስገባት ይችላሉ። ለማውጣት ግን እማኝ አብሮ መገኘት አለበት። ይህ ሁሉ ባንኮች በብሬልም ስለማያስተናግዱ ነው። በአውሮፓ አገራት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ዓይነ ስውራን በራሳቸው ገንዘባቸውን ባንክ ማስገባትም ሆነ ማውጣት ይችላሉ። ሥርዓቱ ተዘርግቷል። አሳታፊ ሕግና ፖሊሲ ቢኖረንም ካልተገበርነው ዋጋ የለውም ብለዋል።

በቀጣይ ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞችን መብት ማስጠበቅ የአንድ ወገን ጉዳይ ባለመሆኑ ከመንግሥት ጋር በሰከነ መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት እና ችገሮችን በመለየት አዋጆችን ሕግ እና ደንቦችን በማሳወቅ የሌላ ሰው ሕይወት እንዳያልፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የአካል ጉዳተኞች ድምፅ በጋራ እንዲሰማ ለማድረግ መዝግቦ መያዝ የአካል ጉዳተኞች መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ያሉ ሥራዎችን የሚሠራው የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አገራችን ከዐሥር ዓመታት በፊት የዓለም ዐቀፍ አካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነት በፈረመችው መሰረት የአካል ጉዳተኞችን መብት ማስከበር የመንግሥት ግዴታ ስለሆነ፣ አሁን በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ እየሠሩ መሆኑን አስቻለው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com