ካፒታል ጋዜጣ የሳይበር ጥቃት ደረሰበት

Views: 256

ጥቃቱ የጋዜጣውን የ21 ዓመታት መረጃ አውድሟል

ካፒታል ጋዜጣ ከ21 ዓመታት በላይ ሲገለገልባቸው የነበሩ መረጃዎችን ማንነታችው ባልታወቁ የመረጃ መንታፊዎች ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸውን ገለፀ። ጥቃቱ ሐምሌ 1 እና 2 የተፈፀመ ሲሆን ከመረጃዎቹ በተጨማሪ የጋዜጣው የዜና ክፍል መገልገያ ኮምፒውተሮችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።
ጥቃቱ ከአገር ውጪ ባሉ መረጃ መንታፊዎች የደረሰ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ መደበኛ ሥራዎችን ለመሥራት እክል በማጋጠሙ አዲስ የመረጃ ስርሃት ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ግሩም አባተ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የጠፉትን መረጃዎችም መልሶ ለማግኘት ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

“ልክ አዲስ እንደሚጀምር ጋዜጣ ሆነናል፣ በዚህም በጣም እየተቸገርን ነው” ያሉት ግሩም “የግል የሚዲያ ተቋም በመሆናችን እና ከገንዘብ ጋር የተገናኘ አገልግሎት ስለሌለን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ጥቃቶች ሲመጡ ከመጠቆም የዘለለ እገዛ አያደርግልንም” ብለዋል።
የሳይበር ጥቃቱ መቀመጫቸውን አሜሪካን አገር ባደረጉ ማንነታችው ባለታወቁ ቡድኖች የተሰነዘረ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ካፒታል ጋዜጣን ያጠቃው ቫይረስ ቡሩሳፍ(brusaf) የተሰኘ ነው። ቡሩሳፍ(brusaf) የኮምፒውተር ቫይረስ በመረጃ መረብ አማካኝነት ጥቃት የሚያደርስ ሲሆን ተጠቂዎቹም ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ይታወቃሉ።

ሐሰተኛ መልዕክቶችን በመላክ እና ምንጫቸው የማይታወቅ የኮምፒውተር መተግበሪያ አቅራቢዎች አማካኝነት በኮምፒተር ውስጥ የሚከቱ ሲሆን ፋይሎችን ከማጥፋት ባለፈ በመቆለፍም ቡድኖቹ ፋይሎቹን ለማስከፈት እና መልሶ ለማግኘት ከተጠቂዎች ገንዘብ በመጠየቅ ይታወቃሉ ።
የዲጂታል መብቶች ተሟጋች የሆኑት ብርሃን ታዬ ሚዲዎች የተለያዩ መረጃዎችን ይዘው በመገኝታቸው ምክኒያት በበርካታ ሀገራት ለሳይበር ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ይገልፃሉ። የሚዲያ አካላት ከመንግሥት፣ ከመረጃ መንታፊዎች ወይም በዘገባዎቻቸው ከሚጠቁ አካላት ሊሰነዘር እንደሚችል ጠቅሰው ከሌሎች ተቋማት ይልቅ ተጋላጭነታቸው ሊሰፋ ችንደሚችልም ተናግረዋል።

ሚዲያዎችም የራሳቸውን መረጃ ብቻ ሳይሆን ከምንጮቻቸው ጋር የሚያደርጓቸውን የመረጃ ልውውጦች እና ሰነዶቻቸውም ሊወሰዱ እንደሚችሉ በመገመት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ይላሉ። “ምንም እንኳን የአገራችን ሚዲያ ውድ የመረጃ መከላከያዎችን ለመተግበር አቅሙ ባይኖራቸውም መሰረታዊ የሚባሉትን ግን መተግበር ከእንዲህ ዓይነት ጥቃት ያድናቸዋል” ሲሉ ይናገራሉ። “የመረጃ ቋታቸውን የሚጠቀሙ ሰዎችን በመወሰን፣ ጠንካራ የይለፍ ቃሎችን በመተግበር፣ ሶፍተዌሮቻቸውን በወቅቱ በማሻሻል እና በተለይም ምንጫቸው የማይታወቅ ፕሮግራሞችን ባለመጠቀም ይህንን መካለከል ይቻላል” ይላሉ።

በሚዲዎች ውስጥ ያለው የመረጃ መለዋወጫ በተለይም ፍላሽ ዲስኮች እና የኢንተርኔት መልዕክቶች ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል። ሚዲያዎች ራሳቸውን ከእንደዚ ዓይነት ጥቃቶች ለመከላከል የራሳቸውን የመከላከያ መንገድ ማዳበር እንደሚገባችው የተናገሩ ሲሆን በሚዲዎች ውስጥ የሚገኙትን የመረጃ ክምችቶችም ሁሉም በሚዲው ውስጥ ያለ ሰው ሊያገኛቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።

የሳይበር ጥቃቱ የታሰበበት እና በካፒታል ጋዜጣ ላይ ያነጣጠረ ከሆነ ኢንሳ ተገቢውን ሥራ ሊሠራ ይገባው እንደነበር ተናግረው በጥቃቱም ካፒታል ጋዜጣ ለ21 ዓመታት ያከማቻቸው መረጃዎች መጥፋታቸው ትልቅ የታሪክ ኪሳራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ካፒታል ጋዜጣ በ1990 የተመሰረተ ሲሆን በአገራችን ኹለት ዐሥርት አመታት ከተሸገሩ በጣት ከሚቆጠሩ የግል ሚዲያዎች አንዱ ነው። በትግስት ይልማ ከፍተኛ የድርሻ ባለቤትነት ሥር የሚተዳድረው ካፒታል ጋዜጣ ትኩረቱን በወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም በቢዝነስ ላይ በማድረግ በሳምንት አንድ ጊዜ እሁድ ለንባብ ይበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com