በትራፊክ አደጋ የወደመው ንብረት ከእጥፍ በላይ ጭማሪ አሳየ

Views: 169

በ2011 የበጀት አመት በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች አማካኝነት የወደመው ንብረት ካለፈው አመት የ815 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን የ113 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ታወቀ።

በ2010 የ720 ሚሊዮን ብር ጉዳት የደረሰ ሲሆን በተገባደደው የበጀት አመት በተለይም የቀላል እና ከባድ አካል ጉዳት የቀነሰ ሲሆን የሞት ቁጥር በ 372 ጨምሮ በ በአንድ አመት ውስጥ የ4010 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ አልፏል። ከባድ የአካል ጉዳትም 5871 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ካለፈው አመት በ0.4 በመቶ ወይም በ 42 አደጋ የቀነሰ ሲሆን አራት ነጥብ ስድስት በመቶ መቀነስ ያሳው የቀላል የአካል ጉዳት አደጋም 5375 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ካለፈው አመትም በ515 አደጋ መቀነስ አሳይቷል።

የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ክትትል ቁጥጥር ባለሙያ ሰብለ አዱኛ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በንብረት ላይ የደረሰው አደጋ ከጨመረበት ምክኒያቶች መካከል ዋናው የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት ደህንነት ማነስ ዋነኛው ነው ብለዋል። የኢትዮ ጂቡቲ መንገድ መበላሸት እና በቂ ክሬን አገልግሎት ያለመኖር ባካባቢው ከነበረው የሰላም ችግር ጋር ተዳምሮ በንብረት ላይ የደረሰውን ውድመት እንደጨመረው ተናግረዋል።

ከፍተኛ የንብረት ጉዳት ከተመዘገበባቸው ክልሎችም አዲስ አበባ ፣ በትግራይ ክልል እና በደቡብ ክልል መሆናቸውን ባለስታኑ አስታውቋል። ባለስልጣኑ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፆ በተለይም በንብረት ውድመት ላይ ግን ዝቅተና ለውጥ መታየቱን ገልጿል። በ10ሺህ መኪና ሚደርሰው አደጋ ወደ 39 ለመቀነስ ታስቦም 41 የደረሰ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ አማካይ የትራንስፖርት መጠበቂያ ሰዓት በ2011ዓመት 13.8 ደቂቃ መሆኑን የባለስጣኑ አመታዊ ሪፖርት ያሳያል።

በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ በ30 በመቶ ይቀንሰዋል የተባለው አዲስ የፍጥነት መገደቢያ ቴክኖሎጂን ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ያስጀመረው ባለስልጣኑ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ 5ሺህ መኪኖች ላይ ቴክኖሎጂውን ለመግጠም መታቀዱንም አስታውቋል። ለናሙና በ10 መኪኖች ላይ የተገጠመው ይህ መሳሪያ ፍቃድ በተሰጣቸዉ 4 ኩባንያዎች አማካኝነት ወደ ሃገር ውስት የሚገባ ሲሆን ከመሸጥ ባለፈ የመጠገን እና መለዋወጫ የማቅረብ አገልግሎትም ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ድርጅቶቹ በባለስጣኑ ፈቃድ የተሰጣቸው እና በየግዜውም የብቃት ክትትል የሚደረግባቸው እንደሆኑም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በማሽኑ ላይ የተፃፈው የባር ኮድ የመኪናውን ሙሉ ማህደር በባለስጣኑ ቋት ላይ ከተመዘገበ በኋላ ለመለየት የሚውል ሲሆን አደጋን ከመቀነስ ባሸገር ለባለንብረቶችም መረጃን የሚሰጥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com