የጎዳና ተዳዳሪዎች በዝቅተኛ ደሞዝ ሥራ አንይዝም አሉ

Views: 233

የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመልሶ ማቋቋም ካሰለጠናቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ሥራ ለመግባት የቀረበልን ደመወዝ ዝቅተኛ ነው በማለት ያለሥራ በካምፕ ውስጥ መቀመጣቸውን አስታወቀ።

ተማሪዎቹ ሰልጥነው ወደ ሥራ ሲገቡ በዝቅተኛው ደሞዝ ማለትም በ1 ሺሕ 700 ብር የሚቀጠሩ ከሆነ በኮካ ኮላ የመጠጥ ፋብሪካ የሚከፈል ሰባት መቶ ብር የቤት ኪራይ ለሰባት ወር ቢዘጋጅም ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ደኅንነት ልማት ማስፋፍያ ዳይሬይክተር እንደሻው አበራ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በመልሶ ማቋቋም ከሰለጠኑ 966 ተማሪዎች ውስጥ 225ቱ በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሠልጥነው የተለያዩ ሥራዎች ከተቀጠሩት ሠልጣኞች ውስጥም ከ1 ሺሕ 700 ብር እስከ 11 ሺሕ ብር ደሞዝ በተለያዩ ድርጅቶች ያስቀጠረ ሲሆን ሥራ ካላገኙ ተማሪዎች በተጨማሪ በዝቅተኛ ደሞዝ ሥራ መጀመር አንችልም ብለው ያለ ሥራ የተቀመጡ ተማሪዎችም እንዳሉ አስታውቀዋል።

የተቀሩት ተማሪዎችም የሥራ ዕድል እስከሚገኝላቸው ድረስ ሙሉ ወጪያቸው እየተሸፈነላቸው ነው ያሉት ኀላፊው “አንዳንድ ተማሪዎች በዝቅተኛ ደሞዝ ሥራ መጀመር አንችልም በማለት ውዝግብ መፍጠራቸው ጋር ተያይዞ ምንም ዓይነት የተለየ ድጋፍ ሊደረግላቸው አይችልም” ብለዋል።

በቆዳ ሥራ፣ በብረታ ብረት እና በእንጨት ሥራ ላይ ከሚሰለጥኑ ተማሪዎች ውጪ በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ሥራ፣ በወለል ንጣፍ፣ በጂፕሰም ሥራ፣ በቀለም ቅብ፣ በብረታ ብረት ሥራ፣ በእንጨት ሥራና መንጃ ፍቃድ በማውጣት ወደ ሥራ የሰለጠኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

የጎዳና ልጆችን ወደ ሥራ በማስገባት እንቅስቃሴ ውስጥ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሥልጠናውን ጨርሰው የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶቹ፣ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ አዲስ አበባ ቄራ ሥራዎች ድርጅት፣ ኮካ ኮላ ኢስት አፍሪካ ግሩፕና አጋር የጥበቃ ሥራዎች ድርጅት ውስጥ እንዲቀጠሩ መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።

በሥልጠናው ውስጥ የተካተቱት ተማሪዎችም በትምህርታቸው እስከ ኹለተኛ ዲግሪ ያላቸውን አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ የቀጠራቸው ሲሆን ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱትንና በየክልሉ ቤተሰብ እንዳላቸው ላስታወቁት 1 ሺሕ 449 ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉን አክለው ገልጸዋል።

ጎዳና ላይ የወደቁና በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍ የማደራጀት ዕቅድ የወጣው፣ ከኹለት ዓመታት በፊት በዓለም ባንክ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሥር እንደሆነ ይታወቃል።

ፕሮጀክቱ በመጀመርያው ዙር አምስት ሺሕ ዜጎችን ለማንሳት ዕቅድ ይዞ 3 ሺሕ 147 የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አረጋውያንን፣ ሠርቶ ማደር የማይችሉ አካል ጉዳተኞችንና የመሳሰሉትን ስምንት ማዕከላት ውስጥ ማስገባቱ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com