“በጸጥታ ኀይሎች ሕይወቱ ስላለፈው ሙሉጌታ ፖሊስ መረጃ አልሰጠንም” ቤተሰቦች

Views: 411
  • ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል

ሰኔ 18/2011 ጠዋት 4 ሰዓት አካበቢ በተለምዶ ሳሪስ አዲስ ሰፈር ድልድይ አካበቢ በሚባለው ልዩ ቦታ በፀጥታ ኀይሎች ሕይወታቸው አልፏል የተባሉትን የሙሉጌታ ደጀኔን ግድያ በተመለከተ መረጃ እያገኙ እንዳልሆነ ቤተሰቦቻቸው ቅሬታ አቀረቡ።

በዕለቱ ኹለት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አድርሰው በመመለስ ላይ ሳሉ ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ኀይሎች በመኪና እንደተከተሏቸውና እሳቸውም ለመሸሽ መሞከራቸውን የሟች ታናሽ ወንድም ዮናስ ደጀኔ ተናግረዋል።

በዕለቱ ሟች ሙሉጌታ እኚህ ማንነታቸውን ያላወቋቸው ኹለት ሰዎች በመኪና ሲከታተሏቸው እንደነበር እና መንገዱ በመዘጋቱም በእግራቸው ወርደው ሊሸሹአቸው ሞክረው እንደነበር ዮናስ ተናግረዋል። “ኮሮላ መኪናውን አቁሞ ነበር። እነሱም ለኹለት ይዘውታል፤ አጥፍቶ ከሆነ እንኳን ለሕግ ማቅረብ ነው እንጂ እርሱን መግደላቸው አሳዛኝ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “የፖሊስ ልብስ የለበሱትን ግለሰቦች እናንተ ውሰዱኝ እነሱን አላውቃቸውም በማለት ደጋግሞ ሲጠይቅ እንደነበር በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ነግረውኛል።”

በዕለቱ ማታ ላይ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሔደው ማመልከታቸውን የሚናገሩት ዮናስ “ጳውሎስ ሆስፒታል ሔዳችሁ ሬሳውን ውሰዱ እና ቅበሩ ከዛ በኋላ መጥታችሁ አመልክቱ ተብለን ተመልሰናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከቀብሩ በኋላም ሔደው ለማመልከት ሙከራ አድርገው እንደነበር የተናገሩት ዮናስ የተለያዩ መረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን እና በሌላ ጊዜ የእነርሱን ቃል እንደሚቀበሉ እንደተነገራቸው አስታውሰዋል፡፡ አክለውም የሟችን መኪና ፖሊሶቹ ይዘውት ሔደው እንደነበር እና በመጨረሻ ግን መኪናውን እንደመለሱላቸው ተናግረዋል።

በሆስፒታልም አስከሬናቸውን መመልከታቸውን ጭንቅላታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማየታቸውን እና በቀኝ ብብታቸው ሥርም በጥይት መመታቸውን ዮናስ ተናግረዋል። ሟችን የገደለው ጥይትም ከእሳቸው ወጥቶ የጓደኛቸውን መኪና በመብሳት እጃቸውን እንዳቆሰለ እና እሳቸውም ታክመው የዳኑ መሆኑንም አክለዋል።
በአካበቢው የነበረው ሰው “ሲቪል የለበሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪዎች” ናቸው የተባሉትን ኹለት ግለሰቦች በመክበቡ “ጥይት ባርቆብን ነው፣ ሰው ገድሎ ነው” የሚል ኹለት ምክንያት በመስጠታቸው እንደለቋቋቸው የዓይን እማኞች ነግረውናል ሲሉ ታናሽ ወንድም ተናግረዋል። አክለውም ወደ ላይ ጥይት ተተኩሶ የተሰበሰው ሰው እንደተበተነም ተናግረዋል።

ሟች የጭነት ማስተላለፍ ሥራ እና የኮሚሽን ሥራዎችን በመሥራት ይተዳደሩ የነበሩ ሰው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት የነበሩት ደጀኔ በሥራ ምክንያት ሊያጠቋቸው የሚፈልጉ ግለሰቦች እንዳሉ ታናሽ ወንድማቸው ተናግረው ከኹለት ዓመት በፊትም ለ15 ቀን አካበቢ ታስርው እንዲቆዩ መደረጋቸውን ገልፀዋል።

ከኹለቱ ግለሰቦች ጋርም የፖሊስ ልብስ የለበሱ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊሶች አብረው እንደነበሩ እና እነሱ ግን ቆሞ ከማየት የዘለለ ሚና እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ጉዳቱን ስላደረሰው ሰው ማንነት እንዲሁም ጉዳዩ ስላላበት ሁኔታ ምንም መረጃ እንደሌላቸው የተናገሩት የሟች ቤተሰቦች ይህንን ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በዋስ ሆኖ ጉዳዩ በምርመራ ላይ መሆናቸውን እንደሰሙ ተናግረወው ማረጋጋጥ ግን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በተዳጋጋሚ ከዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ቢቀበሉም አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com