የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የመሬት ይዞታ ካሳ አዋጅን ተቃወመ

Views: 192
  • “ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር” እንዲቋቋም ጠይቋል

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሐምሌ 30/2011 በአካሔደው ስብሰባ፣ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታዎችን ለሚለቁ የሚከፈል ካሳ ሁኔታን ለመወሰን” የወጣው አዋጅ አደገኛና የዜጎችን መብት ሙሉ በሙሉ የሚገፍ ነው ሲል አስታወቀ።

በተለይም ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች የካሳ ቅሬታ ቢኖራቸው፣ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉት መሬታቸውን አስቀድመው ለቅቀው መሆን እንደሚገባው በአዋጁ መደንገጉ፣ ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑን ያወሳው መግለጫው፣ ለወትሮው ታማኝና ታዛዥ በሆኑ የፖርላማው አባላት ሳይቀር መገሰፁ፣ የሕጉን አደገኛነት ማሳያ ሆኖ አግኝተነዋል ሲል ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 24 ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ እንዲራዘምና የካሳ አዋጁን ማፅደቁ ይታወሳል።

አሁን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬትን በሚመለከት ያለ አድልዖ ይንቀሳቀሳል በሚለው ላይ “የፍትሐዊነት ጥያቄ አለን” የሚለው ሥራ አስፈጻሚው፣ የሚሻለው የሚቀጥለው ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ነገሮች ባሉበት መቆየታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርም ሆነ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የከተማዋን ሕዝብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እየተንቀሳቀሱ አይደለም የሚለው መግለጫው፣ ለዚህም አንድ ዓመት ተራዝሞለት የሥልጣን ጊዜውን ስለጨረሰ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ጠይቋል።

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ በመወያየት፣ አሁን ያለው የአዲስ አበባ አስተዳድር ምክር ቤትም ሆነ ታከለ ዑማን ጨምሮ ያለው አስፈጻሚ አካል የሥራ ዘመኑን ከጨረሰ ኹለት ዓመት የሞላው በመሆኑና የአዲስ አበባ ሕዝብ ውክልናም ስለሌለው ምክር ቤቱና አስተዳደሩ በአስቸኳይ ተሰናብቶ በምትኩ የሕዝቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ “ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር” እንዲቋቋም ጠይቋል።

በአዲስ አበባ ሕዝብ ተሳትፎ በከተማ፣ ክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚቋቋመው “ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር፣” በከተማዋ የፖሊሲና ስትራቴጂያዊ አመራር የሚሰጥ ሳይሆን፣ በመደበኛ ዘርፋዊና የማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ በማተኮር በተጠያቂነትና የኀላፊነት ስርዓት መዋቀር እንዳለበትም አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ፓርላማው ያጸደቀው የካሳ አዋጅ በአዲስ አበባ በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት እስኪመሰረትና ሕዝብ እስኪወያይበት ድረስ ተግባራዊ እንዳይሆን፤ በከተማዋ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አስተዳደር እስኪኖር ድረስ ዜጎችን ከመሬታቸው ማፈናቀልም ሆነ ባዶ መሬቶች ላይ ማንኛውም ዓይነት አዲስ ግንባታና መሬት ምሪት እንዳይካሔድ አሳስቧል።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ አባላት ዘጠኝ ሲሆኑ ለዚህ መግለጫ የተሰባሰቡት ግን ስድስቱ ብቻ ናቸው። ኹለት አባላቱ ኤልያስ ገብሩና በርይሁን አዳነ በእስር ላይ በመሆናቸው በስብሰባው አልተገኙም፤ ምክትል ሰብሳቢው ኤርሚያስ ለገሰም በአሜሪካን ስላሉ ስብሰባውን በስልክ መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል ።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com