በጋምቤላ የማንጎ ምርት መቀነሱ አሳሳቢ ሆኗል

Views: 361

በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የዝናብ እጥረት ማንጎን ጨምሮ በተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ላይ የምርት መቀነስ ማጋጠሙንና ይህም በቋሚ አትክልቶች ላይ ሕይወታቸውን ለመሰረቱ አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ጫናው ከፍ ያለ ነው ተባለ።

የማንጎ ምርቱ በተለይም በወንዝ ዳርቻ ላይ መመስረቱ እና ይህም በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት በየጊዜው የሚያጋጥም የውሃ እጥረት ምርቱን እየጎዳው መምጣቱን የክልሉ የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኡጁሉ ሉላ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም በተወሰኑ የክልሉ ወረዳዎች የማንጎ በሽታ በመከሰቱ ተጨማሪ ጫና መሆኑን ኀላፊው ተናግረዋል።

የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን እንደ ዋና የኢኮኖሚ ምርት ትኩረት ያለመስጠታቸው ዘርፉ ማደግ ያለበትን ያህል እንዳያድግ አርጓል ያሉት ኀላፊው ይህም አርሶ አደሩ የተሸለ ዋጋ የሚያገኝበትን የፍራፈሬ ምርት እንደተጓዳኝ ምርት ማየቱ ዋነኛ ችግር ነው ብለዋል።

በክልሉ ማሽላ እና በቆሎ በዋናነት የሚመረቱ ሲሆን ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሎሚ ደግሞ በተጓዳኝ የሚለሙ ምርቶች ቢሆኑም የተሸለ ገቢን ለአርሶ አደሩ እንደሚያስገኙ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘው መረጃ ያሳያል። ከፍተኛ ምርት በሚመዘገብበት ዓመት አንድ ፍሬ የማንጎ ምርት 3 ብር የሚሸጥ ሲሆን እጥረት ሲያጋጥም እስከ 5 ብር ይሸጣል። በኪሎ የመሸጥ ባሕል እንደሌለ የሚናገሩት ኡጁሉ አንድ ኪሎ ማንጎ እንደ የማንጎው መጠን ከ6 እስከ 10 ፍሬ ይይዛል።

የምርት መቀነሱ ባያጋጥም ኖሮ ከአንድ ሔክታር መሬት ከስድስት እስከ 7 ነጥብ ስድስት ቶን ማንጎ የሚሰበሰብ ሲሆን በያዝነው ዓመት ግን በአማካኝ አምስት ቶን ከሔክታር መሰብሱን ኡጁሉ ተናግረዋል።

የምርት መቀነሱን ለመግታትም ከፍተኛ ትርፋማነት ያላቸውን የፍራፍሬ ምርቶች እንደ ተጓዳኝ ግብርና የመውሰዱ ልምድ ካላስተካከለ እና ዘመናዊ ዘዴዎች ካተተገበሩ የምርት መቀነሱ በተለይም ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያየዞ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ኀላፊው ተናግረዋል። አብዛኛው ሰው ማንጎን ጨምሮ አትራፊ የሆኑትን እነዚህን ፍራፍሬዎች በተለይም ለጥላ ተብለው እንደሚተከሉ እና ፍሬ መስጠት ሲጀምር ወደ ገበያ እንደሚያወጡት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ12 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በማንጎ ዛፍ ለምቶ የሚገኝ ሲሆን በዓመት 180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምርት እንደሚገኝ የዓለም የምግብ ድርጅት ጥናት ያመለክታል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ካለው የአየር ንብረት ምቹነት የተነሳ የማንጎ ምርት በሰፊው የሚመረት ሲሆን ደቡብ ክልል ከ3 ሺሕ ሔክታር በላይ የማንጎ እርሻን በመያዝ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ይገኛል። በኹለተኛ ደረጃ ላይም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኝ ሲሆን 652 ሔክታር መሬት በማንጎ ዛፍ የተሸፈነ ነው። እንደ ማዕከላዊ ስታሲክስ መረጃ ከሆነ የጋምቤላ ክልል የማንጎ ሰብል 180 ሔክታር አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን የትግራይ ክል 118 ሔክታር የማንጎ ምርት አለው።
አቮካዶ 9 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በመልማት በየአመቱ 256 ሺሕ በላይ ኩንታል ምርት ይሰጣል። በ36 ሺሕ ሄክታር ላይ የለማው እና በአገሪቱ ከፍተኛ ምርት በመስጠት ተወዳዳሪ የሌለው ፍራፍሬ ሙዝ በዓመት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል።

የጋምቤላ ክልል የግብርና ኤክስቴንሸን ሠራተኞች በፍራ ፍሬ ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መታሰቡን ኡጂሉ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com