በአማራ ክልል ነባር የድንች ዝርያዎች በበሽታ እየተጠቁ ነው

Views: 139
  • “በለጠ” 281 ኩንታል፣ “ጉደኔ” 210 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ

በአማራ ክልል በተለይም ድንች አምራች በሆነው የምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ነባር የድንች ዘሮች በበሽታ እየተጠቁ ከፍተኛ የምርት መቀነስ ማጋጠሙ ታውቋል።
አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ለክልሉ የግብርና ቢሮ ነባር የድንች ዘሮች ላይ ስላጋጠማቸው የበሽታ መቋቋም አቅም ማነስ እና የምርት መጠን መቀነስ አሳውቀዋል። የክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጥላዬ ተክለ ወልድ (ዶ/ር)፣ በበኩላቸው ለድንች ምርታማነት በክልሉ የድንች ዘር ብዜት እጥረት ዋነኛው ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በኢንስቲትዩቱ ከበሽታ ንጹሕ የሆኑ የድንች ዝርያዎችን በሳይንሳዊ ዘዴ በማባዛት፣ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ ዞኖችና በተመረጡ ደጋማ ወረዳዎች ያልተማከለ የዘር ስርዓትን ለመፍጠር፣ በአርሶ አደሮች ማሳ አዲስ የድንች ዘር የማባዛት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በፈንደቃ ጨጎዴ ቀበሌ፣ በአምስት ሔክታር ማሳ ላይ በቅድመ ማስፋት ያባዛውን “በለጠ” እና “ጉደኔ” የተሰኙ የድንች ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በስፋት ለማቅረብ በመሥራት ላይ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ለሙከራ በተሠራው ሥራም፣ “ጉደኔ” የተባለው ምርጥ የድንች ዘር በሩብ ሔክታር መሬት 42 ኩንታልና ከዛ በላይ ዘር ማግኘት እንደ ተቻለ ተናግረዋል።

እንደ ጥላዬ ገለጻ፣ በአርሶ አደር ማሳ በሔክታር በአማካኝ “በለጠ” 281 ኩንታል፣ “ጉደኔ” 210 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ። በመሆኑም እነዚህን በማስፋትና አዳዲስ ዝርያዎችንም በምርምር በማውጣት የዘር አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው።

በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ተመራማሪና የብሔራዊ ድንች ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዓለሙ ወርቁ በበኩላቸው፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት በድንች ሰብል እንደሚለማ አስታውቀዋል። መሬቱን በምርጥ ዘር ለመሸፈን ከ600 ሺሕ ኩንታል በላይ የድንች ዘር ቢያስፈልግም፣ እስካሁን በምርጥ ዘር እየለማ ያለው መሬት ከሦስት መቶ ሺሕ አይበልጥም ብለዋል።

የመንግሥት ዘር አባዥ ድርጅቶች ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የድንች ዘር አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት እንደሚሠራም አመልክተዋል። የመንግሥትም ሆነ የግል ዘር አባዥ ድርጅቶች እንደሌሎች የሰብል ዝርያዎች የድንች ዘርን ስለማያባዙ ዕጥረቱን ለመቅረፍ ማዕከሉ ከምርምር ሥራው በተጓዳኝ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ዘር እንዲያባዙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com