ሚዲያና የሴቶች ነገር

Views: 575

መገናኛ ብዙኀን ማኅበረሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ፣ ደረጃና አመለካከት በአጠቃላይ አሉታዊ ጅምላ ፍረጃ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተዛባ አመለካከት ሰለባ አድርጓቸዋል ሲሉ ኹለት የቴሌቪዥን መርሃ ግብሮችን ለአብነት የጠቀሱት ቤተልሔም ነጋሽ፥ ይህንን በሚመለከት በተለይ በመገናኛ ብዙኀን ላይ መወሰድ ይገባቸዋል ያሉትን እርምጃዎችንም ጠቁመዋል።

ባለፈው እሁድ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሰይፉ ፋንታሁን ሾው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩን ይዞ ቀርቦ ነበር። ለሥራ አስፈፃሚዋ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፡-

ነገሩ የጀመረው ከአጠራሩ ነው “ፍርዬ” እያለ ሲያናግራት፣ “ፍርዬን ሞቅ አድርጋችሁ ተቀበሏት” ሲል – ወንድ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊ የሆኑ እንግዶቹን በዚህ መልኩ ይጠራ እንደሆን አላውቀኩም። አንድ የሥራ ኀላፊን እንደ ቅርብ ጓደኛ መጥራት ለዛውም ሚዲያ ላይ ግን ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።
የቆይታው መግቢያ አስተያየት የባሕል ልብስ ለብሳ ስለመምጣቷ ሲሆን ገና ቃለ ምልልሱን ሲጀምር የመጀመሪያው ጥያቄ
ጥያቄ – ወይዘሪት ነሽ፣ እንዳውም አንዳንዶች
መልስ – ምን ነካት ይላሉ?
ጥያቄ- እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ስትልኪ አንዳንዶች እዚያ ሥር የሚሰጡትን አስተያየት አንብበሽው ታውቂያለሽ ፣ እንኳን አደረሰን የእኔ ቆንጆ
መልስ – ሳቅ
ጥያቄ – ይሔ አልተመደም፤ ከዚህ በፊት ስንት የኢትዮ ቴሌከም ሥራ አስፈፃሚዎች ሲልኩ መልስ አልነበረም።
መልስ – ሳቅ
ጥያቄ – ያንቺ ይለያል፤ አላገባሽም?
መልስ – አላገባሁም
ጥያቄ – ምነው?
መልስ – አይ – እናስብበት
ጥያቄ – አለ?
መልስ – ፕሮጀክት እናድርገው እንዴ? እሱንም፣ በአዲሱ የበጀት ዓመት (ሳቅ)
ጥያቄ – የግድ ማግባት አለብሽ እያልኩ አይደለም፣ ሁሉም ነገር በሰዓቱ ይሆናል። አለሽ ወይ ባል?
መልስ – ለጊዜው የለም፤
ጥያቄ – ይመጣል፣ በራሱ ሰዓት
መልስ – አዎን ይመጣል
ጥያቄ – ወይዘሪት ነሽ አሁን፣ ወይዘሮም ስትሆኚ ትመጫለሽ እዚህ
መልስ – አዎ! እመጣለሁ።
ጥያቄ- ብዙ ጊዜ ለሥራ ነው ጊዜሽን የምትሰጭው
መልስ – አዎ!
እንዳያችሁት የውድ አየር ሰዓቱን ሦስት ደቂቃ ስለጋብቻ ሁኔታዋ በመጠየቅና ለማሳፈር በመሞከር አሳልፎታል።
በዚሁ ቢያበቃ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ቆይታው ቀጥሎ ከዐሥራ አምስት ደቂቃ በላይ ስለ ሌሎች የሥራ ጉዳዮች ተወርቶ ስለዋና ሥራ አስኪያጇ ብዙ ሰምተን፣ ስለሥራው፣ ስለአስተሳሰቧ፣ ስለሕይወት፣ ስለዓለም፣ አርዓያ ስለመሆን፣ ለሰው መልካም ነገሮች ስለማድረግ፣ ክብር ስለመስጠት፣ ብዙ የሚያወያዩ ነገሮች ስታወራ፣ ምናልባት ለሰው ቅርብ የሆነ በቀላሉ መግባባት የሚችል ባሕርይ እንዳላት ስንረዳ ቆየን።
ጠያቂው ሰይፉ አለማግባቷን ጠቅሶ ያቀረበው ጥያቄ ቢመለስም ነገሩ የከነከነው በሚመስል ሁኔታ በኋላ ላይ መልሶ ጉዳዩን ለማንሳት ስለራሱ ልጅ ካወራ በኋላ
“ያንቺስ ልጅ ፍርዬ የእኔ ማማ ናት የምትለው መቼ ነው ነው ያልኩሽ” ሲል ጠየቃት
መልስ – እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲመጣ
ጥያቄ – እያሰብኩ ነው አሁን 43 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ትመሪያለሽ ፣ 15 ሺሕ ቋሚ ሠራተኛና 18 ሺሕ ጊዜያዊ ሠራተኛ ትመሪያለሽ፣ ይሔ ቀላል አይደለም፤ ይህንን ሁሉ መምራት የግል ሕይወትሽ ላይ ትኩረት እንዳታደርጊ ያደረገሽ ይመስለኛል።
መልስ- እዚህ ጋ እውነት ለመናገር በዚህ ኢትዮ ቴሌኮምን በፍፁም አላማርርም፣ ምክንያቱም ይሔ የእኔ የግል ድክመት፣ የራሴን ኩባንያ ስመራ ሰባት ዓመት እንደዚሁ ነው የነበርኩት፣ የግሌን ሥሠራም አምሽቼ እሠራ ነበር፤ ደካማ ጎኔ ነው አስተካክላለሁ ብያለሁ
ጥያቄ – ሰው ሥራውን አግብቶ አይኖር ዘንድ ግድ ይላል
ስለዚህ አለማግባቷ፣ ለዚያ የሕይወቷ ክፍል ትኩረት አለመስጠቷ የራሷ ስህተት እንደሆነና ማስተካከል እንዳለባት እስክታምን ደጋግሞ አንስቶባታል። በተረፈ ስለ ሥራዋ በብቃትና በስፋት አስረድታ፣ ቀለል ያለች ሰው ሰው የሚሸት ስብዕና ያላት መሆኗን አስመስክራ የወረደች ናት።
ለዛሬ ምሳሌዬ ኢቢኤስ ላይ ያየኋቸው ምሳሌዎች ስለሆኑ ይህ የሆነው በአጋጣሚ መሆኑን አንድ ምሳሌ ልጨምር፤-
ቀደም ብሎ ከኹለት ሳምንት በፊት የተላለፈውን ቅዳሜን ከሰዓት የተሰኘው ሌላው የቴሌቪዥን ጣቢያውመርሃ ግብር እንዲሁ ስቱዲዮ ወጣት እንግዶች ታዳሚዎች ተጋብዘው አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ለማድረግ ሲሞከር እንዲሁ ቁጭ ብዬ ፕሮግራሙን ለመከታተል ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። የውይይቱ አጀንዳ ለከፋ ነበር።

ኹለቱ የፕሮግራሙ አቅራቢዎች የራሳቸውን ሐሳብም ጨምረው ተወያዮችን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲቀበሉ ቆዩ። ከተወያዮቹ ጥቂት የማይባሉት ወጣት ሴቶችን ጨምሮ መለከፍ ደስ እንደሚላቸው ዘንጠው መውጣታቸውን እንደሚያሳይ ሲናገሩ፣ አንዳንድ ሴት ወጣቶች (ሴቷን አቅራቢ ጨምሮ) ሴቶችም ወንዶችን እንደሚለክፉ ሲናገሩ ጭምር ተመልክቻለሁ። በበኩሌ የወንዶችና የሴቶች ተላካፊነት ለንጽጽር የተናጋሪዎቹን አላዋቂነት ከማሳየት በዘለለ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብዬ አላምንም። ጥቂቶች (ወንዱን አቅራቢ ጨምሮ) መለከፍ የሰው መብት መጋፋት እንደሆነና ተገቢም እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ይህ አስተሳሰብ ችግር ያለበት የሚሆነው ሴቶች ልጆች መደነቅንና አካላዊ ውበትን ዋጋ እንዲሰጡ፣ ከላይ እንዳለው ምሳሌ ሁሉ የሕይወታቸው የመጨረሻ ግብና ስኬት ወንድ ማግኘት፣ ማግባት፣ እናትነት ብቻ እንደሆነ የሚደነግገውን የማኅበረሰቡን አስተሳሰብና ልማድ ለማረጋገጥ የሚሠራ መሆኑ ነው። ማግባት አለማግባት የግለሰብ ምርጫና ፍላጎት ሆኖ ሳለ በተለይ ሴቶችን አለማግባታቸውን እንደጉድለትና በሥራው መስክ ያስመዘገቡትን ስኬት መና እንደቀረ አድርጎ መሳል ተገቢ አይደለም።

ከዚህም ሌላ በጎዳና ላይ የሚደረግ ጾታዊ ትንኮሳ የሴቶችን በሰላምና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንደሚገድብ፣ ከዚህ ባለፈ በንግግር ብቻ እንደማይቆምና ወደ ጉንተላ ብሎም አካላዊ ጥቃት እንደሚያድግ አለመረዳት፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎችን እንዲታረሙ ሳይሆን በድርጊታቸው እንዲገፉበት የሚያበረታታ ነው። ሴቶች ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የተረጋገጡላቸውን በነፃነትና ያለ ተጽዕኖ መንቀሳቀስ መሥራት ከወንዶች እኩል በመሠረተ ልማቶችና በሥራ ቦታዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ የመጠቀም መብት የሚጋፋም ጭምር ነው።

በአጠቃላይ የውይይቱ ዓላማ ምን ነበር የሚለውን ማየት እስኪያዳግት ምንም አቅጣጫ የሌለውና በነባራዊ ሁኔታው በተለይ የመንገድ ላይ ለከፋ በሴቶች ሥነ ልቦናና ራስ መተማመን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ያቃለለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ሚዲያ አስተሳሰብን በመቅረጽ፣ የምናምንባቸውን እሴቶችና አመለካከቶች ትክክል እንደሆኑ አድርጎ በማጽናት ፣ ያለውን እውነታ በሚመለከት ሰዎች በሚዲያ የሚታየው የእውነተኛው ዓለም ወካይ እንደሆነ እንዲያምኑ በማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ሚዲያ በተለያዩ ሴቶችን በሚመለከት ከራሳቸው ከጋዜጠኞቹ በሚጀምር አሉታዊ አመለካከትና ጅምላ ፍረጃ ምክንያት ሴቶች ሊኖራቸው የሚገባቸውን ስፍራና መብት በመርሳት ማኅበረሰቡ በሚሰጣቸው ጠባብ ቦታና የተለመደ ደረጃ ላይ እንዲቆዩ በማበረታታት፣ ትክክለኛ ያልሆኑ አስተሳሰቦች እንዲቀጥሉ በማድረግ አሉታዊ ሚና ሲጫወት ይስተዋላል። ይህም ሴቶች በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ወደ ኋላ እንዲቀሩ የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል።

ከላይ እንደጠቀስናቸው ያሉ ምሳሌዎች በግልጽ ሴቶችን የሚሰድቡና በአገሪቱ ያለውን ሴቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ የማምጣት ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ አቀራረብና በሴቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችና ተሳትፏቸውን የሚጎዱ እንደ ለከፋ ያሉ ባሕሎች ትክክል እንደሆኑ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ሲያደርጉ እንደ ተለመደ ነገር የመውሰድና የእርምት እርምጃዎች ሳይወስዱ መቅረት ይስተዋላል።

ማኅበረሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታና ደረጃ እንዲሁም ያለው አመለካከት ጋዜጠኞችን ጨምሮ የዚሁ የተዛባ አመለካከት ሰለባ መሆናቸውና በተለይ በኀላፊነት ቦታዎች ላይ ሴቶችን የሚመለከቱ አሉታዊ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ሲቀርቡ ትክክል አይደለም የሚሉ የሥርዓተ ፆታ ግንዛቤና አተያይ ያላቸው ሰዎች አለመኖራቸው እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳል።

ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ፆታ ትምህርት ክፍል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን አምስት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች መካከል አንዷ ብቻ ሴት የነበሩ ሲሆን በአጠቃላይ በፕሮግራም ኀላፊነት፣ በቡድን መሪነትና በተለያየ አመራር ደረጃ ካሉ 149 የሥራ ኀላፊዎች መካከልም ሴቶቹ 22 ብቻ ነበሩ።

በቴሌቪዥን መዝናኛ ፕሮግራሞችና በኤፍኤም ራዲዮ ሥርጭት ላይ ተመስርቶ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየውም የሚዲያው አቀራረብ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎና የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ የሚያጎላ አይደለም። ይልቁንም የወንዶች ጥገኞች እንደሆኑ፣ ተጎጂና ተጋላጭ እና በትናንሽ ሥራዎች ላይ ብቻ የሚሠማሩ አድርጎ ያሳያቸዋል። ሴቶች የመገናኛ ብዙኀን ዘገባዎች ርዕስ ሆነው የሚቀርቡበት ጊዜ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር ሲቀርቡም በአሉታዊ ጎናቸው ብቻ ይታያሉ። በተለይ በፊልም፣ በሙዚቃ ቪዲዮዎችና ተዛማጅ የመዝናኛ ፕሮግራሞች አካል በሆኑ ውጤቶች ላይ ሴቶች እንደ ከዳተኛ፣ የማይታመኑ፣ የራሳቸው ዓላማና ግብ የሌላቸው ተደርገው ይሳላሉ።

በሴቶች ላይ የተሳሳተ ዘገባ የሚያቀርቡ የመገናኛ ብዙኀን ሥራዎች እንዲቀንሱ ለማድረግ ዋነኛው መፍትሔ መሰል ዘገባዎች ሲቀርቡ ማጋለጥ፣ አልፎም ይህንን ለመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን እንዲውቀው ሪፖርት ማድረግ፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ይህ አመለካከት ትክክል አለመሆኑ እንዲታወቅ ቅስቀሳና በመገናኛ ብዙኀን ኀላፊዎች ላይ ይህንን አሠራር የሚቆጣጠር የሥርዓተ ጾታ ተኮር ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው። በአዲሱ ጸረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ ሴቶችን እንደቡድን መስደብ የተከለከለ መሆኑም ሌላ ድጋፍ ሊሆን ይችላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. እነዚ የሴት መብት ተከራካሪ ነን ብለው የሚያስቡ የበታችነት የሚሰማቸው ዱክማን ሌዝቢያኖች ሴቱ ሁሉ እንደነሱ ሁነው ማየት ነው ምኞታቸው! ሴቱን ሁሉ በህግ ስም ፈት አርገው ሲጨርሱ አሁን ደሞ ገና ያላገቡ እህቶቻችንን እንደነሱ ሽል ሃሳብ ማራገፊያ እያረጓቸው ነው! እነዚ የነጭ ፈንድ ምንደኞች እንደ በቀቀን የሠፈሩላቸውን ካልተፉ ሌላ ስራ ሰርቶ መኖር ስለማይችሉ ነው ኢሄን ቆሻሻ የገለማ ሐሳብ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚተፉት

This site is protected by wp-copyrightpro.com