በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ምስክሮች መስማት ተጀመረ

Views: 735

በቀዳማዊ ኀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ተገንብቶ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ያገለገለው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ ውበቱን እንደጠበቀ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንጻር ችሎቶቹ ጠባብ የሚባሉ ቢሆኑም በወለሉ እና በጣሪያው መካከል ያለው ርቀት ዳኞቹን ጨምሮ ማንንም ሰው አሳንሶ እና ችሎቱን አግዝፎ የማሳየት አቅም አለው፡፡

በችሎቱ ባሉት ደረቅ አግዳሚ ወንበሮችም ላይ ከበሩ በስተግራ ባለው ረድፍ ላይ ቢጫ የማረሚያ ቤት ልብስ የለበሱ ተከሳሾች ተጠጋግተው ተቀምጠዋል፡፡ የቀረውን የችሎቱን ቦታም ቤተሰብ እና የማረሚያው ጠባቂዎች ተሞልቶ፣ በዳኞች ግራ አቃቤአን ህጉ እንዲሁም በግራ የተከሳሽ ጠበቆች ተደርድረዋል፡፡
በቦታ እጥረት ወደ አዳረሹ መግባት ያልቻሉ የተከሳሽ ቤተሰቦች ከችሎት አስከባሪ ፖሊሶች እና እስረኛ ይዘው ከመጡ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ጋር ሲጨቃጨቁ መስማት የተለመደ ነው፡፡

ብቻ እንደምንም 100 ሰው ገደማ አጨናንቃ ከያዘችው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ የወንጀል ችሎት በነ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ ተከሰው በማረሚያ ቤት ባሉ የቀድሞ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረቦች ላይ ከጠዋት አንስቶ እስክ አመሻሽ የሚሰማው ምስክርነት ረዝም ያለ ነው፡፡ ከአንድ መቶ በላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች በሚሰሙበት በዚህ መዝገብም በመጀመሪያው ቀን ውሎ አራት ምስክሮች ተሰምተዋል፡፡ በመሃል ተከሳሾች ወደ መፀዳጃ መሄዳቸው አይቀርም፡፡

በየመሃሉ የሚወጡት የቀድሞው የደህንንት መስሪ ቤቱ ባልደረቦች በወጡ ቁጥር ኮፊያ እያደረጉ መውታታቸው ከሰብሳቢ ዳኛው በረከት ሰይፉ በስተግራ የሚቀመጡትን ዳኛ ግራ ያጋባ ይመስላል፡፡ ችሎቱም የአራቱን ምስክሮች ቃል ሰምቶ ካጠናቀቀ በኋላ ቀጣይ ቀጠሮ ለመስጠት ተከሳሾች እና ጠበቆች ቆመው ሳሉ ዳኛው ግራ በተጋባ ሁኔታ አንድ ጥያቄ ጠየቁ፡፡

‹‹ተጠርጣሪዎች በሙሉ ኮፊያ ይዛችኋል፣ ወደ ውጪ በወጣችሁ በገባችሁ ቁጥርም እሱን ታደርጋላችሁ፣ ይሄ ነግ ብርድ ነው ወይስ ሌላ ነገር አለ›› አሉ፡፡ ከጎልማሶቹ ተከሳቾች መሃል ወጣት የሚባሉት አንድ ሰው ‹‹መናገር የምፈልገው ነገር አለኝ›› ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ‹‹ በግቢው ውስጥ ባለጥቁር መስታወት የምናውውቸው የተቋሙ መኪኖች አሉ፡፡ በተጨማሪም በጠዋቱ ክፍለ ግዜ ሁለት የምናውቃቸው ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች በዚህ ችሎት እንደነበሩ አይተናል፡፡ በዛ ላይ ሽንት ቤት ስንሄድም ይከታተሉናል፡፡ ስለዚህ ነው ኮፊያ የምናደርገው›› ሲሉ ተናገሩ፡፡

ዳኛ በረከትም በተረጋጋ መንፈስ ሆነው ማስረዳት ጀመሩ፡፡ ‹‹ የዋስትና መብታችሁን ከልክሎ ማረፊያ ቤት እንድትቆዩ ያደረገው ይሄ ችሎት ነው፡፡ ስለዚህ ለደህንነታችሁ ሃላፊነት ይወስዳል፡፡ ማንኛውም ሰው ይህንን ግልጽ ችሎት የመታደም መብት ቢኖረውም ከዚህ ጉዳይ ጋር ግንኙነት ያለው ምስክር የሆነ ሰው እዚህ ተቀምጦ የምስክሮችን ቃል የሚሰማ ከሆነ በህግ የሚጠየቅ ይሆናል፡፡››

አክለውም ተከሳሾች መጨረሻ ላይ ነፃም ይሁኑ ጥፋተኛ ዋናው ነገር ህገ መንግስቱ፣ ሌሎች ህጎች እንዲሁም የዳኞች እውቀት በፈቀው ልክ በህግ እና በህግ ብቻ መዳኘት አለባቸው ብሎ ችሎቱ እንደሚምን ማስረዳት ጀመሩ፡፡ ‹‹መብቶቻችሁ ሳይሸራረፉ እንዲፈፀሙ እንፈልጋለን፣ ይህ ማለት ደግሞ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በህግ ብቻ መዳኘት ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አደጋ ነው ስለዚህም ይሄ ነው የምትሉት ሰው ካለ ከጠበቆቻችሁ ጋር ተነጋግራችሁ ማመልከቻ ማስገባት ትችላለችሁ›› በማለት ዳኛው እጅግ ረጋ ባለ ድምፃቸው ተናግረው አበቁ፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ እንድ መርማሪ ፖለሲ ከምስክሮች ጋር ሆኖ ወደ ችሎት መግቱን ተናግሮ ይህም ግቢውን ምስክሮች ስለማያውቁ አብሯቸው እንደሆነ እና እነሱን ተከትሎ ችሎት ሲገባም አቃቤን ህጎቹ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ገለጹ፡፡

ምስክር አንድ
ሃምሌ 23/2011 የአቃቤ ህግ የሰው ማስረጃ ሆነው ምስክርነታቸውን ከሰጡ አራት ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ግለሰብ በድምፃችን ይሰማ የሙስሊሞች ተቃውሞ ምክኒያት መያዛቸውን አስረድተው በምሽት በደህንነት ሰዎች ከመንገድ ላይ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የረመዳን ጾም መግባቱን ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ከስራ ወደ ቤታቸው በመሄድ ላይ ሳሉ በኮሮላ መኪና የደህንነት ባልደረቦች እንደያዟቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ከከፍለ ሃገር ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ አንድ አመት እንኳን አልሞላኝም ነበር፡፡ በዛ ላይ ትዳር ከያዝኩ ዘጠነኛ ቀኔ ነበር፡፡ አንድ ሰው ወረደና ከኋላ ያዘኝ፣ ላስለቅቀው ስሞክር በቦክስ መታኝ እና ሌቹም ሆነው አፍነው ወደ መኪናው አስከቡኝ፡፡ ከዛም ገንዘብ ፈልጋችሁ ከሆነ ያለኝን ወሰዱና ልቀቁኝ ስላቸው እኛ ያንተን ገንዘብ አንፈልግም ደህንነቶች ነን አሉኝ›› ሲል ጀርበውን ለታዳሚው ሰጥቶ በዳኞች ፊት ለፊት የተቀመጠው የመጀመሪየው ምስክር ይናገራል፡፡

ከኋላ ሶስት ከፊት ሁለት የሆኑት ግለሰቦች በውስጥ ለውስጥ መንገድ ካዞሯቸው በኋላ ጫካ ውስጥ ይዘዋቸው መሄዳቸውን የሚያስረዱት ምስክሩ አንዱ ግለሰብ ሽጉጥ አውጥቶ እንዳስፈራራቸው እና መሃመድ የሚባል ሰው ጋር ያላቸውን ቀጠሮም ቀድመው እንደሚውቁ የሚናገሩት ምስክሩ ከዛም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መታሰራቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ለሊት ዘጠኝ ሰአት ገደማ ላይ ከፖሊስ ጣቢያ ይዘውኝ ወጡ፣ ተረኛ ጠባቂውም መውሰድህን ፈርም ሲላቸው ሳይፈርሙ ይዘውኝ ወጡ፡፡ ለሊቱን በመሉ ሰፈር ለሰፈር ካዞሩኝ በኋላ አህመድን እየጠበኩህ ነው ብዬ እንዳዋራው ተደረግሁ፡፡ ስልኬ ላይ ባለቤቴ እና ጓደኞቼ ይደውሉ ነበር›› ያሉት ምስሩ ጨምረውም ከዛ በኋላ እሳቸው በሚመሰክሩባቸው ግለሰብ ትዛዝ ሰጪነት ተፈጽሞብኛል ስላሉት ድርጊት ማስረዳት ጀመሩ፡፡

ከዛ ቀደም ብሎ ችሎቱ የሚመሰክሩባቸውን ግለሰብ ያውቁ እንደሆን ቆመው በግምት ወደ 40 ከሚሆኑ እና ሁሉም ቢጫ የማረሚያ ቤት ልብስ ከለበሱ ጎልመሶች መሃል እንዲያሳዩ ተጠይቀው ግፋ ቢል ለአንድ ደቂቃ ከፈለጉ በኋላ በእጃቸው ከጠቆሙ በኋላ በድጋሚ ለታዳሚው ጀርባ ሰጥተው ተቀመጡ፡፡

ከፖሊስ ጣቢያ ከወጡ በኋላ ሌላ ቦታ ተወስደው መታሰራቸውን ተናግረው ‹‹ሙሉ ለሊት ራቁቴን በረንዳ ላይ አስተኝተውኝ በርሜል ሙሉ ያደረ ውሃ እየተደፋብኝ በቀበቶ ስገረፍ አደርኩ፡፡ ይህ ሲፈፀም ደርበው ቢሮአቸው ነበሩ እዛም ቃሌን የሚቀበሉት እሳቸው ናቸው፡፡›› ምስክሩ ተከሳሽ እንዴት ሃላፊ መሆናውን አወቁ ተብለው በፍርድቤት ማጣሪ ጥያቄ እንዲሁም በጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ በተጠየቁ ወቅት ‹‹አብረውኝ የሚያድሩ ጠባቂዎች አለቃ ቢሮ እንወስድሃለን ይሉኝ ነበር፣ የሃላፊ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ነው የሚያናግሩኝ እንዲሁም የአለቃ ግርማ ሞገስ ነበራቸው›› ብለዋል፡፡ ‹‹በምተኛበት ክፍል ውስጥ በምገረፍበት ግዜ እጃቸውን አጣምረው ያዩ ነበር፡፡ በጥቅሻም በሉት እያሉ አንድገረፍ ትዛዝ ይሰጡ ነበር›› ብለዋል፡፡

ጦር ሃይሎች አካባቢ መታሰራቸውንም ያወቁት ተከሳሽ በስልክ ‹‹ጦር ሃይሎች ነኝ›› ሲሉ በመስማታቸው መሆኑን ተናግረው የሚያድሩበት ክፍል ውስጥ ሁለት ግለሰቦች በግራ እና በቀኝ አብረዋቸው እንደሚያድሩ እና በፌስቡክ ተገደው ንግግር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹እኔን የፈለጉኝ አነጋገሬ እንዳይቀየር ነው እንጂ የምላላከው ሃሳብ በሙሉ እነሱ የሚያዙኝን ነበር፡፡ ለ24 ሰአት የማይለዩኝ እነዚህ ሰዎች አንድ አፍታ ጥለውኝ ሲወጡ ለማዋራው ሰው ተገድጄ ነው ብዬ ነገርኩት እሱም ግንኙነቱን አቋረጠ›› ሲል አንደኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ያስረዳል፡፡

‹‹ከዛም ለ 3ወር በካቴና ታስሬ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰድኩ እና አንድ ክፍል ተቀመጥኩ፡፡ ፀሃይ የለም፣ እስረኛ የለም፣ ቤተሰብ የለም፡፡ በመንግስት ላይ የምታሴሩት ምንድነው? ማነው ወረቀት የሚበትነው? በፌስቡክ ከውጪ መልክት የሚልክልህን ልጅ አምጣ? ሼክ ኑሩ ላይ ግድያ ፈጽመሃል እየተባኩ ነበር›› የሚሉት ምስክር ተከሳሽ መትተውኝ ባያውቁም ለደረሰብኝ ነገር በሙሉ ትዛዝ ሲሰጡ ግን ነበር ብለዋል፡፡

የእስር ግዜአቸውን 2 ወር ከ 20 ቀን በጦር ሃይሎች ቀጥሎም 3 ወር ከ 10 ቀን በሌላ በማውቁት ቦታ ታስረው መቆታቸውን በማስላት ለሁለት የሚከፍሉት ምስከር በሁለተኛው ክፍል የሚጠየቁት ጥያቄ ሌላ መልክ መያዙን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት ጀመሩ፡፡

‹‹ኋላ ላይ ጥያቄአቸው ተቀይሮ ምስክር እንድሆን ተደረግኩ፡፡ ተገድጄም እንደመሰክር ተደረጌ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ተገድጄ የሰጠሁት የምስክርነት ቃል ነው ብዬ የመከላከያ ምስክር ሆኜ ለፍርድ ቤቱ በድጋሚ መስክሬአለሁ›› ሲሉ ተናገሩ፡፡

ማስታወሻቸውን ይዘው ወደፊት የመጡት ተከሳሽ ራሳቸው መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ‹‹ አንተ ለተቋሙ የአጋዥ ስራ ስትሰራ አልነበረም? ካርድ ማን ነበር የሚሞላልህ? የቤት ኪራይ ይጨመረልኝ ብለህ አልነበረም? ይሄ ለውጥ እስኪመጣስ ለመንግሰት ስትሰራ አልነበረም?›› ብለው ተከሳሽን መጠየቅ ሲጀምሩ ምስክሩ ወደ ኋላ ዞረው ተከሳሽን ከተመለከቱ በኋላ ሞቅ ያለ ሳቅ ሳቁ፡፡ ሶስቱም ዳኞች በቁጣ ‹‹ ስነ ስርአት›› ሲሉ አስቆሟቸው፡፡

‹‹የተጠየቁትን ይመልሱ›› ሲሉ የመሃል ደኛው በረከት ተናገሩ፡፡ ከመንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እዳልነበራቸው፣ በላፕቶፑም ሲዲኤምኤ ራሳቸው መረማሪዎች ይዘው እንደሚመጡ እና ንግግሩም የእሳቸው ሳይሆን የመርማረዎቹ መሆኑን አክለው የሚቀበሉት ካርድም ሆነ ደመወዝ እንዳለነበረ ገለፁ፡፡

ምስክሩ አክለውም ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከጓደኘቾቻው ጋር እንደኖሩ ተናግው ከጥቂት ግዜ በኋላም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ቤት መከራየታቸው እና በአንድ ሻይ ቅጠል ፋብሪካ ውስጥ የሺያጭ ባለሞያ ሆነው በመስራት እንደሚተዳደሩም አብራሩ፡፡ ለፍርድ ቤቱ የማጣሪ ጥያቄ መልስ የሰጡት ግለሰቡ ተከሳሽ በሃላፊነታቸው ምክኒያት በሰጡት ትዛዝ ሰብአዊ መብቶቻቸው መጣሳቸውን እና እንደ ሃላፊነታቸውም ሊከላከሉላቸው እንዳልቻሉ በማስረዳት የምስክርነት ቃላቸውን ጨረሱ፡፡

ምስክር ኹለት
ከሰዓት በተሰየመው ችሎት የተሰሙ ሶስቱም ምስክሮች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ አማካኝነት በተጀመረው ምርመራ ምክኒያት በደህንነት መሰሪያቤቱ ባልደረቦች ደርሶብናል ስላሉት የሰብአዊ መብት ጥሰት አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪየው የግል ተበዳይ ማታ 11 ሰዓት እራት እየተመገቡ ሳሉ ተጠርተው ወደ ምርመራ ክፍል መወሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ጎልማሳው ግለሰብ የሚመሰክሩባቸው ሰው በእስር ቤት ውስጥ ሌላ ስም ያላቸው መሆናቸውን ገልጻው በምክርነታቸው ወቅትም በማረሚያ ቤት ያሉ መርማሪዎች የሚጠራሩባቸውን ስሞች ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡ ‹‹በኮድ ስም ነው የሚጠራሩት፣ ከቤዎች፣ አሌክሶች፣ ጀለስ እና ፍሬንድ እንጂ በትክክለኛ ስማቸው አይጠራሩም›› የሚሉት ምስክሩ ተከሳሽንም አበበ ቶሎሳ በሚባል ስም እንደሚያውቋቸው ገለጸው ነጋ ካሳዬ የሚለውን ስምም ከእስር ከተፈቱ እና ለፖሊስ የደረሰባቸውን ነገር ካመለከቱ በኋላ ትክክለኛ ስማቸውን እንዳወቁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ወደ ምርመራ ክፍል ሲወስዱኝ ከጎን ባሉት የምርመራ ክፍሎች ውስጥ ሰዎች ሲጮሁ ሰማኛል፣ አራት ወይም አምስት የሚሆኑ ፖሊሶች በግምት አራት በ አራት በምትሆነው የቆርቆሮ ክፍል እየጠበቁኝ ነበር፡፡ ወንበር ላይ አስቀምጠው ቃልህን በአግባቡ ስጥ አለበለዚያ ከእነዚህ ጎረምሶች እጅ አትተርፍም፣ አንድ ሽማግሌ ሞተ ብለን ሪፖርት ማድረግ ነው ሲሉ አስፈራሩኝ፡፡ የማረሚያ ቤቱን ለማቃጠል አራት መቶ ሺህ ብር ተቀብለሃል፣ ገንዘቡን የት አረከው አሉኝ፡፡ እኔ እንኳን አራት መቶ ሺ አራት ሺ ብር ቆጥሬ አላውቅም ደሞዜ ራሱ ሁለት ሺህ ብር ነች አልኳቸው፡፡ ከዛ ከወንበር አውርደው በካቴናዬ ላይ ሲባጎ ከተው ጣራው ላይ ሰቀሉኝ፡፡ ከዘም እንዱን እግሬን ከበሩ ጋር አስረው ዥዋ ዝዌ ይጫወቱብኝ ጀመር፡፡››

ከምሽቱ ሁለት ሰአት ከተሰቀሉበት መውረደቸውን የሚናገሩት ምስክር ‹‹ጥቁር መሳሪያ አለቻቸው በሷ ኤሌክተሪክ ሾክ ከሰአት ማሰሪያ በታች ነጋ ትዛዝ ሾክ ተደርጌ እስካሁንም ጠባሳው አለ፡፡ በሁቱም እጄ ላይ በዚህ ማሽን በኤክትሪክ ሾክ ተደርጌአለሁ›› በማለት ለችሎቱ ለማስረዳት የጃኬታቸወን እጀታ መሰብሰብ ተያያዙ፡፡

ሁለተኛ የአቃቤ ህግ ምሰክር ተከሳሽክ ‹‹ ልክ መደብደብ ስጀምር በል አሁን ክላሲካል አሰማ፣ ይሄንን ማሳመን አቃትቹ ሌላ ልቀይርላችሁ፣ በቃ እሱ እዚህ እንደተንጠለጠለ ራት ብሉና ኑ ይሉ ነበር፡፡ ከዛም ወጥተው ሲገቡ ጣውላ ይዘው መጡ፣ የተሰበረ ሚስማር ላዩ ላይ ነበረው፣ አውራ ጣቴን መቱኝ፣ ተረከዜም በሚስማሩ ደማ አውራ ጣቴም ተሰበረ፡፡ በቦክስ የተመታሁበተም አራት ጥርሴ ረግፏል፡፡ ከዛ አወረዱኝ እና አዳራሽ ውስጥ ታሰርኩ፡፡ አይጥ ወረረኝ፣ ከአልጋ ጋር ነበር ለ10 ቀን አዳራሽ ውስጥ የታሰርኩት›› በማለት የሚናገሩት ምስክሩ ከዛም ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳት ከሰረሰባቸው ሰዎች ጋር አብረው በታሰሩ ግዜ የሚያስታውሷቸውን ሰም መጥራት ጀመሩ፡፡ ከምርመራ በኋላ በአንድ ላይ ከታሰሩት መካከል አንዱ በድብደባ ህይወቱ እንዳለፈ አና የሚመጣ ቤተሰብ ካለም ንገሩ መባላቸውን ይገልፃሉ፡፡

‹‹ጃፓን በዜጎቿ ሞራ ሳሙና ሰራች፣ እናንተ ደግሞ አገራችንን ከሰል ሰራች አስባለችሁን የሃገራችንን ስም አጠፋችሁ እንባላለንም›› ሰሉ ገለጹ፡፡ ለሁለት ታስረን ነው የምናድረው፣ ሽንት ቤት ስንሄድም ለሁለት ታስረን ነው ሽንት ቤት ስንሄድ በሰልፍ እየተደበደብን ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ታዲያ የአሁን ተከሳሽን በማአከላዊ በሽብር ተከሰው ሲገቡ ቀድመው በአይን እንደሚውቋቸው በሸዋ ሮቢትም ‹‹አሁን እንደ ማእከላዊ ሸውደህን አታልፈም ብሎ ያስፈራራኝ ነበር፡፡ ዛቻ አዘል መክርም ከድብደባ በኋላ ይመክረኝ ነበር፡፡ ለምን ትሞታለህ? ለምን አታምንም? እንደ በፊት አይደለም? እያለ ይናገር ነበር፡፡››
ፍርድ ቤትም በቀረቡ ወቅት የደረሰባቸውን ጉዳት በመግለፃቸው ምክኒያት 37 ሰዎች ለሶስት ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በጨለማ ቤት መታሰራቸውም ሁለተኛ ምስክር ያስረዳሉ፡፡ ምስክሩ በተደጋጋሚ ሁለቱ ኮማንደር አለማየሁዎች እና ስንታይሁ ናቸው የሚደበድቡን በማለት ይናገራሉ፡፡ ተከሳሽም ቀድሞ በተከሰሱበት የሽብር ክስ ኗ ወጥተው ሊለቀቁ ሲሉ አስቀርተው እንዳቆዩአቸው እና ለመገረፍ በተሰቀሉ ግዜም አብረው እንደሰቀሏቸው ተናግረዋል፡፡

ሦስተኛ ምስክር
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጤና ኮሚቴ ሃላፊ በመሆናቸው ለቃጠሎው የሚሆኑ መልክቶችን በማቀባበል ወንጀል ፈፅሜአለሁ ብለህ እመን ተብለው በሸዋ ሮቢት ድብደባ እንደደረሰባቸው ሶስተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ይናገራሉ፡፡ ለእነ በቀለ ገርባ እና ለእነ በቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ጋር መልክት አስተላልፈሃል መባላቸወን ያነሳሉ፡፡
የተደበደቡበትን መንገድ ማስረዳትም ሲጀምሩ ‹‹ ነጋ ሪፈር ነህ አሉኝ እኔ ሌላ ቦታ መስሎኝ ነበር ለካ ድበደባ ነው›› ማለት ተከሳሽ አድርሰውብኛል ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰት በአቃቤ ህግ ዋና ጥያቄ መሪነት በቻሉት መጠን በአካላቸውም በማስረዳት ጀመሩ፡፡

‹‹ሁለት ወንበር አለ፣ ካቴና እንዳደረኩ በመሃሉ ዱላ ተደርጎ ተሰቀልኩ፡፡ ጭንቅላቴ ወደ መሬት እግሬ ወደሰማይ እንዲሆን አደረጉ፡፡ ከዛ በኋላ የውስጥ እግሬን በሽቦ መግረፍ ጀመሩ፣ አፍ እና አፍንጫዬንም ሲረግጡኝ ነበር›› ሲሉ ሳቅ በቀላቀለ መንገድ ‹‹ በህዳሴው ብላቸው በባነዲራው አልሰማ አሉኝ›› ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ምንም ብላቸው አልሰማ ሲሉኝ እሺ እፈርማለሁ አልኳቸው፣ ምን እንደሰጡኝ ራሱ ሳላይ ፈረምኩላቸው፡፡››

ከዛም የተመረመሩ ሰዎች ወደታሰሩበት ክፍል መወሰዳቸውን እና በዛ ክፍልም አንድ ጎድኑ የተሰበረ ልጅን ጨምሮ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤንም እዘው ክፍል ውስጥ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ፊት አይታይም፣ አይኑ እየደማ ነበር፣ አሸናፊ የሚባለው ደግሞ የታሰረበት ገመድ ስጋው ውስጥ ገብቶ ነጭ ስጋው ይታይ ነበር›› በማለት አስረድተዋል፡፡ እሳቸውም የሚመሰክሩባቸውን ነጋን እንደሆን ተጠይቀው ቢያዩ እንደሚያውቋቸው ተናግረው ከተጠርጣሪዎች መካከል ፈልገው አሳይተዋል፡፡ የእስር ቤት ስማቸው ሌላ እንደሆነ ተናግረው የመዝገብ ስማቸውን ግን ፖሊስ ፎቶ ካስመርጣቸው በኋላ መረዳታቸውን እና በማበራዊ ሚዲያም መከታተላቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥቅምት ስድስት ለምርመራ ወስደውኝ የነበረ ሲሆን የገባንባቸው የምርመራ ክፍሎችም የተሰቀለ ሰው ስለነበር መለሱኝ›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኳን የምርመራው ቀን ለእንድ ቀን ቢሆነም ተከሳሽ ካዘዙ ለሌት እያወጡ እንደሚደበድቧቸውም አስረድተዋል፡፡ ‹‹እኔ ደህንነት መሆናቸውን የሰማሁት ከአሮሚያ ከመጡ ሰዎች ነው፣ እነሱ ያውቋቸዋል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አራተኛ ምስክር
አራተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር በቂሊንጦ ተከሰተ በተባለው የእሳት ቃጠሎ ምክኒያት ወደ ሸዋ ሮቢት መወሰዳቸውን እና እሳቸውም እስርቤቱን ‹‹ገንጥለው ወደ ኤርትራ በመሄድ በግንቦት ሰባት ውስጥ ሰልጥነው ኢትዮጲያን ለማመስ በሚል አምነው ቃላቸውን አንዲሰጡ መገደዳቸውን እና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥቶች እንደደረሱባቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹የምርመራ ክፍል ከወሰዱኝ በኋላ አንድ እግሬን በካቴናው ላይ አድርገው እንድቆም ሲያዙኝ ከወንበሬ ላይ ተነስቼ በካቴናዬ ላይ ስሞክር አልቻልኩም፣ ከዛም የፎረንሲኩ ካሳሁን በመቶኝ ጣለኝ›› ያሉት ምስሩ ‹‹ቸርነት፣ ቻይና እና ጆኒ የሚባሉ መርማሪዎች ቶርች ገለበጡኝ›› በማት ለአቃቤ ህግ ዋና ጥያቄ መልስ መስጠት ጀመሩ፡፡ ‹‹ኤርትራ ከማን ጋር ለመሄድ አስበህ ነው ሲሉ ጠየቁኝ፣ እምነትህ ምንድነው ሲሉ ጠየቁኝ ከድምፃችን ይሰማ ታሳሪዎች ጋር ሊቀላቅሉኝ፡፡ ከማስረሻ ሰጤ እና ከብርሃኑ ነጋ ጋር ግንኙነት አለህ ሲሉኝ ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ነው የማውቀው ነገር የለም ስላቸው፣ ቶርች ገልብጡት የማያምን ከሆነ ውጪ ግንድ ላይ እሰሩት ይሉ ነበር፣ ከዛ እኔም ከምሞት ብዬ አመንኩላቸው፡፡››

ከምረመራ በኋላ ስለገቡበት ክፍል የሚያስረዱት ምስክሩ የእጃቸውን ክፍሎች በማሳየት በክፍሉ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ሰዎች ላይ ስላዩት ጉዳት አብራርተው በተለይ አንድ ግለሰብ እጃቸው ከመቁሰሉ ሽታ ጭምር እንደነበረው እና ሌሎቹም ግለሰቦች የተሰቀሉበት እግራቸው አብጦ መመልከታቸውን ለችሎቱ ተናግዋል፡፡ አክለውም አንድ ግለሰብን ለጅብ ለማስበላት ተሞክሮ እንደነበረም ያስረዳሉ፡፡

ከጠዋጡ 2 ሰአት እስክ ምሽቱ አራት ሰአት አካበቢ ተሰቅለው መደብደባቸውን ተናግረው ‹‹ በድብደባ መሃል እረፍት ሰአት አለን ፊታችን ላይ ውሃ ይደፋሉ፣ ከሚደፈው ውሃ ምላሳችን ላይ ጠብ ትላለች›› ሲሉ ወገባቸውን ባንድ እጃቸው ይዘው በሌላው የምስክር መቀመጫ ሳትጥኗን ጠርዝ ተደግፈው ምስክሩ ይናገራሉ፡፡ በአካላቸው ላይ ያለውን ጠባሳም ለችሎቱ ለማሳየት እጃቸውን ከፍ ያደርጉ ነበር፡፡ ‹‹ከ 40 እስከ 50 ደቂቃ ይሰቅሉናል ከዛ ያወርዱናል፣ መልሰው ደግሞ ሰቅሉናል›› ብለዋል፡፡

ከምርመራ በኋላ በሚቆዩበት ማረፊያ ክፍል ማታ ማታ ላይም ካቴና እንደማይፈታላቸው ገልፀው አንዳንዶች ከአልጋ ጋር ሌሎች ደሞ ለሁለት ለሁለት ታስረው እንደሚድሩም የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ቀን ቀን የአልጋው ካቴና ይፈታል የእጃችን ግን አይፈታም›› ብለዋል፡፡

በምስክረነቱ መሃልም በሚተኙበት ክፍል ውስጥ ጉዳት ስለሚደርሱባቸው ሰዎች ማንነት እንደሚነጋገሩ በማስረዳት ላይ የነበሩት አራተና ምስክር ‹‹ወንጀሎኙቹ›› የሚል ቃል መጠቃማቸውን ተከተሎ ዳኛ በረከት ንግግራቸውን አቋረጧቸው፡፡

‹‹ያልተገባ ንግግር ነው፣ ስሜታዊ አትሁኑ ወንጀለኛ የሚለው ቃል ያልተገባ ነው›› በሚል ማስጠንቀቂያ አመሻሽቶ የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ቀን የምስክርነት ውሎ በፍርድ ቤቱ ማጣሪያ ጥያቄ በሰጡት መልስ ተጠናቋል፡፡

ተጠርጣሪዎችም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ኮፍያቸውን በማጥለቅ ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሰው የሄዱ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ለእረፍት እስከሚዘጋ ድረስም ምስክር የመስማት ሂደቱ ይቀጥላል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com