ረቂቅ የምርጫ ሕጉ እና ሴቶች “እኩል ውክልና ከሌለ ድምጽ አንሰጥም ብንልስ?

Views: 288

የምርጫ ረቂቅ ሕጉን መነሻ ያደረጉት ሩት ሰለሞን፥ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም መስክ ለማረጋገጥ እያደረገች ያለችውን ጅምር ጥረት በማድነቅ የሴቶችን መብቶች ለመጠበቅ በሕገ መንግሥቱ የተካተቱትም ሆነ አገሪቱ ፈርማ ያጸደቀቻቸውን ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች መከበር እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ሩት ረቂቅ የምርጫ ሕጉ እነዚህን መብቶች ጥበቃ እያደረገላቸው ነው ወይ በማለት ይጠይቃሉ፤ መጪው ምርጫ በወንድሞቻችን መካከል ብቻ ፉክክር የሚታይበትና የሴቶች ውክልናን ወደ ኋላ የሚያስቀር እንዳይሆን ሲሉም ሥጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ ሴትም ሆነ ወንድ እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የመሳተፍ መብት እንዳለው ይገልጻል። የሴቶች መብቃትና ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲሁም ሴቶች በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸው ደረጃ መሻሻል ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የመንግሥት አስተዳደር ለማምጣት እንዲሁም በሁሉም የሕይወት መስኮች ላይ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ሆኖም ሴቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ ማነቆ የሚሆንባቸው የተዛባ የኀይል ግንኙነት ከግል ሕይወታቸው እስከ ሕዝብ ተሳትፏቸው በየደረጃው ተገቢውን ተሳትፎ እንዳያደርጉ ገደብ ሲጥልባቸው ቆይቷል። በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሴቶች እና የወንዶችን እኩል ተሳትፎ ማረጋገጥ ሚዛናዊና የማኅበረሰቡን ስብጥር በትክክል የሚያንጸባርቅ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚረዳ ሲሆን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጠናከርና በተገቢው መንገድ እንዲተገበርም ያግዛል።

በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ የተዛባ ውክልና መኖር በመንግሥት ፖሊሲ አሠራር እና በእኩልነት መርህ መካከል እውነተኛ ውሕደት እንዳይኖርም እንቅፋት ይሆናል። በፖለቲካ ውስጥ የሴቶች እኩል ተሳትፎ መኖር ሴቶችን የማብቃት እንዲሁም ፍላጎታቸውን የማካተት አጠቃላይ ሒደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በዚህ ረገድ የሴቶች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እኩል ተሳትፎ ማድረግ፣ የፍትሕና ዲሞክራሲ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሴቶችን ፍላጎት ለማካተት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ሊታይ ይገባል። የሴቶች የነቃ ተሳትፎ ከሌለ እና የሴቶች ዕይታ፣ የሕይወት ልምድና በፆታቸው ምክንያት ሊኖራቸው የሚችለው ከወንዶች የተለየ ፍላጎት በሁሉም የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ውስጥ ካልተካተተ፤ የእኩልነት፣ የልማት እና የሰላም ግቦች ሊሳኩ አይችሉም፤ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትም እንዲሁ ሊረጋገጥ አይችልም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገራችን የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም መስክ ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጅምር ጥረት ማድነቃችን እንዳለ ሆኖ በፖሊሲና በሕግ ላይ አንዳንድ ክፍተቶች ስናይ እነኝህ ሰዎች (አዎን በወንዶች የበላይነት የሚመሩት አንዳንዴም ሴቶች የሚሳተፉባቸው መዋቅሮች) እውነት የዚህች አገር ሴቶች ጉዳይ እንደ ጉዳይ ይታያቸዋል ማለታችን አይቀርም። መቼስ ሴቶች የአገር ዕጣ ፈንታ በሚወሰንበት ፓርላማ ውስጥ ያላቸውን ውክልና በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊም መልኩ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችለውን ሰሞኑን ይፋ የሆነውን ረቀቅ የምርጫ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንመለከት – They do not really care about us – ስለኛ ግድ የላቸውም የሚለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እንቃጣለን። እነሱ እነማን ናቸው? ሕጉን ያረቀቁት፤ የተወያዩበት፤ ፓርላማ ያስገቡት በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ወይ አንዳቸውም ‘ኧረ ይሔን ነገር ስለ ሴቶች ምንም ያለው ነገር የለም፣ አስቡበት’ ያለም የለም ወይም ያሉም ካሉ ድምፃቸው በአብላጫው ታፍኖ ቀርቷል። ወክለናችሁ ፓርላማ እንገባለን የሚሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው የፓርላማ መቀመጫ የማግኘትን ጨምሮ ሌሎች የሚያሳስቧቸው ነገሮች እንዳሉ ግልፅ ነው።

ከሚያሳስቧቸው ነገሮች ውስጥ የሴቶች እኩል ውክልና አንዱ አለመሆኑ ደግሞ ያሳስባል። በኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ፣ (ፈቃድ የሚለው ይሰመርበት ምክንያቱም የአገሪቷ ሕገ መንግሥትም ሆነ ተከታይ ሕጎች ሊታደስ ያለውን የምርጫ ሕግ ጨምሮ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በተለይም ቢያንስ የፓርላማ ውክልና ከሰላሳ በመቶ እንዳያንስ የሚደነግገው ምንም ነገር የለም) ባለፉት ዓመታት የሴቶች ውክልና አንድ ምርጫ ወደ ሌላ ምርጫ ከሚያሳቅቅ የኹለት በመቶ ውክልና ይበል ወደሚያሰኝና በሌላው አገርም አድናቆት የሚያስቸር 38.8 በመቶ ውክልና አድጓል። ይህ የሆነው ግን ባለፉት ምርጫዎች ምናልባት ከአንደኛው በቀር መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የፓርላማ ወንበሩን ተቆጣጥሮት የቆየው ኢሕአዴግ የሴቶች ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብሎ ለፓርቲው ባስቀመጠው ኮታ መሠረት የተገኘ ነው። እንደምንመኘው ቀጣዩ ምርጫ እውነተኛ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ቢፈጥር የሚኖሩት የተለያዩ ፓርቲዎች ምን ያህል ሴቶችን ያሳትፋሉ የሚለው አሳሳቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው። የሚቀጥለውን ምርጫ ለማካሔድ የሚረዳው ረቂቅ ላይ ያለው የምርጫ ሕግ ከላይ የጠቀስነው የኢሕአዴግ 30 በመቶ ውክልና እንዲጨምር አይደለም (ቢያንስ 50 በመቶ መሆን እንዳለበት እናምናለን) ካለበት እንዳይወርድ እንኳን የሚረዳ አንቀጽ የለውም። “ሴት እጩ ለሚያመጡ ፓርቲዎች የገንዘብ ማበረታቻ የሚሰጠውስ አንቀጽ?” ትሉ ይሆናል፤ የሴቶች እኩልነት ላይ ጽኑ አቋም እና እምነት የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት ጊዜያት አንቀጹን እንዴት እንደተጠቀሙበት የሚታወቅ ነው።

አገሪቷ ከገባቻቸው የዓለም ዐቀፍ እና አሕጉራዊ የሰብኣዊ መብትና ሌሎች ስምምነቶች እንዲሁም ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጭ፤ ይሄ ረቂቅ ሕግ የሴቶችን እኩል ተሳትፎ እና ተወካይነት በሚያረጋግጥ መልኩ የማረም ግዴታ በመንግሥት ላይ መሆኑ ይታወቃል። መቼስ አገራችን የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ቃል የምትገባባቸው ስምምነቶች ብዛትና የስምምነቱ አንቀጾችም የሚደነግጉት ቃል ሲታይ እንደረቂቅ ምርጫ ሕጉ ወሳኝ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎች ሲወጡ ያ ቃል ተረስቶ ባላየ የሚታለፉበት መንገድ አስገራሚ ነው ያስብላል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አካል ካለው አዎንታዊ እና ጠንካራ ውክልና የማሳደግ ጥረት አንጻር ቁጥራዊ ውክልናው ጎሽ ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን በራሱ እንኳን ወደ ፊትስ ይሔ እንደሚቀጥል ምን ዋስትና አለ?

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ደግሞ በአንቀጽ 35 (3) ላይ ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው፤ በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በዚህ በኩል ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ በፖለቲካ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩርት መስጠት ነው። ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ አገሪቷ ፈርማ ያጸደቀችው በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ዓለም ዐቀፍ ስምምነት አንቀጽ ሰባት ይህን ይላል። ይህን ስምምነት የተቀበሉ አገሮች ሴቶች በአገሪቱ የፖለቲካና ሕዝብ ነክ ሕይወት ውስጥ የተሟላ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚያሰናክል ልዩነትን ለማጥፋት ተገቢ እርምጃዎችን ሁሉ ይወስዳሉ።

በተጨማሪም ሴቶች ከወንዶች እኩል የሚከተሉትን መብቶች መጎናፀፋቸውን ያረጋግጣሉ፣
ሀ)በሁለም ምርጫዎችና ውሳኔ ሕዝብ ድምጽ የመስጠትና ለማናቸውም በሕዝብ ለሚመረጡ መንግሥታዊ አካላት ዕጩ ተመራጭ የመሆን መብት፤

ለ)የመንግሥት ፖሊሲን በመቅረጽና በማስፈጸም ሒደት ውስጥ የመሳተፍ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን የመሆን፤ በማናቸውም የመንግሥት ዕርከን ውስጥ ኀላፊነትን ተረክቦ የመሥራት መብት፣

ሐ)በማናቸውም የአገሪቱ የፖለቲካና የሕዝብ ሕይወት በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማኅበራት ውስጥ የመሳተፍ መብት።

ይሔ መብት በረቂቅ የምርጫ ሕጉ ላይ እንዴት ጥበቃ ተደረገለት ነው ጥያቄው። አሁን በተያዘው አካሔድ መጪው ምርጫ በወንድሞቻችን መካከል ፉክክር የምናይበት፤ የሴቶች ውክልናን በተመለከተ ወደ ኋላ የምንራመድበት እንዳይሆን ያሰጋል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ ዜጋ ሴቶች በሆኑበት፤ የአገሪቷ ዕጣ ፈንታ የጥቅሟም የጉዳቷም ያልተማከለ ገፈት ቀማሽ ሴቶች እና ሕፃናት በሆኑበት ሁኔታ አገሪቷ ከፍተኛ የሕዝብ ሥልጣን ያለበት እንዲሁም የሞት የሕይወት ውሳኔ በሚወሰንበት ፓርላማ ውስጥ እንደውም ከሃምሳ በመቶ ውክልና በታች አያዋጣም። ባለፉት ምርጫዎች ሴቶች በነቂስ ወጥተው የመራጭነት መብታቸውን ሲጠቀሙ እንደቆዩ የታወቀ ነው። በሌላውም አገር እንደሚታየው ውክልናቸው በአግባቡ ባይረጋገጥም እንኳን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሔድ ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

ነገር ግን የመምረጥና የመሳተፍ ታማኝነታቸውን ለማይወክላቸው ፓርቲና እውቅና ለማይሰጣቸው የፖለቲካ ሥርዓት እየሰጡ የሚቀጥሉት እስከመቼ ነው። እኔን የሚመስል፣ የአገሪቱን ግማሽ ዜጋ፣ በአገራችን ሁኔታ 50 ሚሊዩን የሚሆኑትን ሴቶች የሚወክል አሠራር ድጋፌን ሊያገኝ ይገባልን? የሚለውን እያሰቡ፤ ያለውክልና ድምጽ የለም ሊሉ ይገባል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com