የቴሌኮሙ ድርሻ ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድ እየተጠና ነው

Views: 726

የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለገበያ በሚቀርብበት ወቅት ለሕዝብ የሚቀርበው አክሲዮን ላይ የተለያዩ አማራጮች ቀርበው በመጠናት ላይ እንደሆነ ታወቀ። ይህ ድርሻ የአገሪቱ የአክሲዮን ገበያ በሚቋቋምበት ወቅት ለሕዝብ የሚተላለፍ ሲሆን እስከዛ ግን መንግሥት በአደራ እንደሚያስተዳድረው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልፀዋል።

ከቀረቡት አማራጮች መካከልም ለገበያ ይወጣል ከተባለው 49 በመቶ ውስጥ የተወሰው በመንግሥት አደራ ይቀመጥ የሚለው አንዱ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች መንግሥት እስከ 49 በመቶ የሚሆነውን የቴሌኮሙን ድርሻ ለገበያ ያቀርባል በሚል ሲገለጽ የነበረ ሲሆን ይህም የመጨረሻ ጣሪያው እንጂ ምን ያህል ይሆናል የሚለው እንዲሁም ለትልልቅ ኩባኒያዎች የሚሰጠው ኮታ ላይ የተገለፀ ነገር የለም፡፡

ኹለተኛ አማራጭ ሆኖ የተያዘው በመንግሥት እጅ እንደሚቆይ ከተነገረው 51 በመቶ ላይ የተወሰነውን የካፒታል ገበያው ወደ ተግባር ሲገባ ለሕዝብ የሚቀርብ ይሁን የሚለው ሲሆን ይህም በሒደት መንግሥት በቴሌኮሙ ላይ የሚኖረውን የከፍተኛነት ድምፅ የሚያሳጣ ይሆናል። የአክሲዮን ገበያውን ለማቋቋም መንግሥት ሥራ የጀመረ ሲሆን በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

የአክሲኦን ገበያውን በተመለከተም የተለያዩ አስተያየቶች የሚነሱ ሲሆን የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎችን ለኹለት በመክፈል ሲያከራክር ቆይቷል። የመንግሥትን ሐሳብ የሚደግፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት የሕግ ማነቆዎች ከተነሱ ገበያውን በአጭር ጊዜ ማቋቋም የሚያስችል መሰረተ ልማት አለ።

በሌላ በኩል ክቡር ገናን ጨምሮ የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች እንደሚሉት የአክሲዮን ገበያው መንግሥት እንዳለው በ2012 የሚጀመር ሳይሆን የዓመታት ሥራ የሚጠይቅ ነው። እንደ ክቡር አስተያየት አንድ ድርጅት ከ3 እስከ 4 ዓመታት ተከታታይ ትርፍ ያስመዘገበ ካልሆነ ወደ አክሲዮን ገበያው መቀላሉ የማይመስል ነው ብለው ይህንን የሚያሟሉት ግፋ ቢል ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ናቸው ሲሉ ይሞግታሉ።

በአንድ ዓመት ውስጥ ይመሰረታል ለተባለው አዲስ አበባ የአክሲዮን ገበያ መሰረታዊ የሕግ ማሻሻያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነ ሲገለፅ ቆይቷል። ክቡር እንደሚሉት በሌላውም አገር የተለመዱ የሚባሉት መስፈርቶችን የሚያሟላ ድርጅት ማግኘት ከባድ መሆኑን ጠቅሰው አቅም ያላቸው እንኳን ፍላጎታቸው ምን ያህል ነው ሲሉ ይጠይቃሉ።

ቴሌኮሙ ለውድድሩ ምን ዝግጅት እያደረገ ነው?
ኢቲዮ ቴሌኮም በዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬ ሕይወት ታምሩ የአንድ ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርቱን ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 ይፋ ባደረገበት ወቅት የሚመጣውን የገበያ ውድድር ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለፈው አንድ ዓመት ዝግጀት መደረጉን አስታውቋል። እንደሥራ አስፈፃሚዋ ገለጻ ድርጅቱ ላለፉት 7 ዓመታት ያሉትን አላቂ ንብረቶች ቆጥሮ እንደያማውቅ ነገር ግን በያዝነው 2011 ግን ይህ ቆጠራ ተደርጎ መጠናቀቁ ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ ነው። አክለውም የድርጅቱን ገፅታ ለማሻሻል እንዲሁም ለገበያ በሚቀርብብት ወቅት አግባብ ያለው ዋጋ እንዲያወጣ የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ቴሌኮሙም የሠራተኞቹን አቅም በማሳደግ ለሚመጣው ውድድር ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የገለጹ ሲሆን ለሠራተኞቹ ዓለማቀፍ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት የብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ማድረጉንም ተናግረዋል። በተጨማሪም ለሠራተኞች የቤት እና የመኪና ብድር በማመቻቸት የትራንስፖርት እና የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል ውሳኔ ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

“ኢቲዮ ቴሌኮምን የሚያክል ትልቅ ድርጅት እስከዛሬም ከዚህ የተሸለ የቤት አቅርቦት ሊኖረው ይገባ ነበር። ሠራተኞቻችን ደንበኛ እንዲያረኩ እንጠይቃለን እነርሱ ግን ደስተኛ አልነበሩም፤ ደስተኛ ያልሆነ ሠራተኛ ይዞ ደስተኛ ደንበኛን መፈለግ ዘበት ነው። ሰው ተኮር ተቋም የመቅረፅ ዓላማ ይዘን እየተቀንቀሳቀስን ነው” በማለት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሠራተኞቻቸውን፣ ደንበኞቻቸውንና አጋሮቻቸውን መሰረት ያደረገ ሰው ተኮር ፖሊሲ መተግበሩን አስታውቀዋል፡፡

እስከተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በተሰበሰው መረጃ ቴሌኮሙ ያለው ቋሚ ሠራተኞች ብዛት 15 ሺሕ 646 ሲሆኑ የሴት ሠራተኞች 28 በመቶ እንዲሁም የወንድ ሠራተኞች ቁጥር 72 በመቶውን ይይዛል። የቴሌኮሙን መሰረተ ልማት የሚጠብቁ 18 ሺሕ ቋሚ የጥበቃ ሠራተኞች እንዳሉት አስታውቋል።

“የቴሌኮም መሰረተ ልማት አሁን ባለንበት ዘመን በቀላሉ በሌላ ቴክኖሎጂ ሊተካ የሚችል ነው። ለእኛ የማይተካ መወዳደሪችን ብለን የምናስበው ግን የሰው ኀይላችንን ነው” ያሉት ሥራ አስፈፃሚዋ የአገራችን ሁኔታ፣ የደንበኞችን ፍላጎች እንዲሁም የኢንዱስትሪውን ጸባይ የሚረዱት ሠራተኞቻችን ቴሌኮሙ ተመራጭ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጉታል ብለው እንደሚምኑም ተናግረዋል። “እየመጣ ካለው ውድድር አንጻር ብቁ ሠራተኞችን ማፍራት ካልቻልን እና ያፈራናቸውንም መያዝ ካቻልን ኩባንያውን ለማስቀጠል ትልቅ ችግር ሊገጥመን ይችላል” ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ለተሠሩ ሥራዎችም በተለይ ከቦርዱ በተሰጠው ሙሉ ነፃነት አማካኝነት እንደሆነ የተናገሩት ፍሬ ሕይወት “ተቋሙ ለይስሙላ ማኔጀመንት ያለው ቢመስልም በውጪ ካሉ የተለያዩ አካላት ጫና ይደረግበት ነበር” ብለዋል። አያይዘውም የቀድሞው የቴሌኮሙ የቦርድ ሰብሳቢ በቅርቡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተደድር ሆነው የተሾሙት ተመስገን ጥሩነህ ለከፍተኛ አመራሩ ከሰጡት ነፃነትም ባሻገር ቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ሲያደረጉ ነበርም በማለት ምስጋና ቸረዋቸዋል፡፡

ቴሌኮሙ ከስትራቴጂያዊ አጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በመቻሉ ካስገኛቸው መልካም ነገሮች መካከል በአሜሪካ እና በቻይና መሃል በተፈጠረው የንግድ ጦርነት ቴሌኮሙ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ እንዲሁም በቢሾፍቱ፣ አዳማ እና ሞጆን ጨምሮ በኤሪክሰን ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ መደረጉ ተጠቅሷል።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል በተገባው እሰጥ አገባ ተጠቂ የሆነው ሁዋዌ ቴክኖሎጂ የቴሌኮሙ አጋር እና የአገሪቱን ቴሌኮም መሰረተ ልማት በመዘርጋት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ፍሬ ሕይወት ከድርጅቱ ጋር በቅርበት ሊደርሱ ስለሚችሉ ጉዳቶች እና መውጪያ መንገዶቻቸው እንዲሁም ጉዳቶቹን እንዴት መጋራት እንደሚቻል ሥራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

አዲሱ አመራር ሥራውን ሲረከብም ኤሪክሰን የጀመራቸውን እና ከ3 ዓመታት በፊት አጠናቆ ማስረከብ የነበረበትን ሥራዎች ጥሎ ለመውጣት ወስኖ እንደነበር ተናግረው ከረጅም ድርድር በኋላ ሥራዎቹን እንዲያጠናቀቅ በመደረጉ በተለይም ከቢሾፍቱ ጀምሮ በደቡብ ክልል እሰከ ጅማ የያዘውን ሥራ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ እንዲያከናውን መደረጉን ተናገረዋል።

በተያዘው ዓመት የሞባይል ድምጽ አገልግሎት ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻር በ11 በመቶ የቀነሰ ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ደግሞ የ74 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። የኢንተርኔት ገቢ ከአጠቃላይ ገቢው ላይ ሲሰላ 29 በመቶ ድርሻን ሲይዝ 29 በመቶው ኢንተርኔት የተገኘ ሆኖ ተመዝግቧል። በዓለማፍ ደረጃም ጤነኛ የሚባለው የቴሌኮም ዕድገት የድምፅ አገልግሎቱ ሲቀንስ እና የኢንተርኔት ፍላጎቱ ሲጨምር እንደሆነ ፍሬ ሕይወት ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የታሪፍ ቅናሽ ያካሔደው ቴሌኮሙ በበጀት ዓመቱ 36.3 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢዎች የሰበሰበ ሲሆን 98.3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከዓለም ዐቀፍ አገልግሎት ገቢ ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥም ያልተጣራ ትርፍ 24.5 ቢሊንዮ ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸርም የ5.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ለዓመታት ያልተከፈለ 4.7 ቢሊዮን ብር ግብርን ጨምሮ በአጠቃላይ 16.2 ቢሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም አስታውቋል።

ቴሌኮሙ ለውድድር ራሱን ከማዘጋጀት ባለፈ የቴሌኮሙን ድርሻ መንግሥት ለገበያ የማቅረብ ሐሳብ መያዙን ተከትሎ የተከማቹ ችግሮችን የማጥራት ሥራ እንደተሠራም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል። ከነበረበት ዕዳ ላይም 9.9 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን የብድር ክፍያ ሒደትም ድርጅቱን እና አገሪቷን ባጋጠመው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መፈጸም ሳይቻል መቅረቱን ጠቅሰው የዚህ ዓመት ክፍያ ለዓመታት የተጠራቀመ ውዝፍ የማጥራት ሥራ ነበርም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመንግሥት ንብረትን ወደ ግል የማዞር ሒደት ምን ይመስል ነበር?
መንግሥት በአሁን ወቅት ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዛወር ከወሰናቸው እንደ ቴሌኮም እና ሌሎች መሰረታዊ የአገልግሎት ሰጪ ዘርፎችን የማሸጋገር ውሳኔዎች ባይሆንም ባለፉት 28 ዓመታት ውስጥ ከ370 የማያንሱ የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል ዘርፉ አዘዋውሯል። ለዚህም ለውጥ ኢሕአዴግ በ1983 ሥልጣን በተቆጣጠረ ማግስት የኢኮኖሚ መርህ ለውጥ እና የደርግ አገዛዝ የወረሳቸው ዘርፈ ብዙ የግሉ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች ያስነሱትን ጥያቄ እንደመሰረት ተደርጎ ይወሰዳል።

ከዚህ እርምጃ ተጠቃሚ የሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የግሉ ዘርፍ ተዋንያኖች ቢኖሩም ቀላል የማይባሉትን ድርጅቶች የገዙት እንደ ሚድሮክ ግሩፕ፣ የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (ትዕምት ወይም በተለምዶ ኤፈርት ተብሎ የሚጠራው) እና በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥር የሆነው ጥረት ኮርፖሬት ነበሩ። ይህ በኅብረተሰቡ ዘንድ ወደ ግል የማዘዋወር ሒደት ጥቂቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ ያለፈ ሚና የለውም የሚል እሳቤ የፈጠረ ሲሆን በሌሎች ዘርፎች ላይ የታየው ውጤታማ እንቅስቃሴ ደግሞ ተቃራኒ የሆነ እሳቤ ፈጥሯል።

ወደ ግል ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ከተላለፉ የመንግሥት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የቢራው ዘርፍ ነው። የቢራ ፋብሪካዎች ወደ ግል ድርጅቶች ከተላለፉ በኋላ ከ30 በመቶ በላይ ሠራተኞች በመቀነሳቸው ወቀሳ ቢደርስባቸውም የቢራ ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ለምጣኔ ሀብቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ፈጠሩትም መነቃቃት እንደ ብሮድካስትና ንግድ ያሉ ሌሎች ዘርፎች ማደግ ምክንያት ሆኗል። በዐሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሥራ ከመፍጠርም በላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ግብር በመክፈል የመንግሥት ገቢ እንዲጨምር ምክንያት ሆነዋል።

የቢራ ፋብሪካዎቹ ወደ ግል መዘዋወራቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ከፍተኛ ፉክክር እና የኢንዱስትሪ መነቃቃት አዳዲስ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተመሰረቱ ፋብሪካዎች ወደ ገበያ እንዲቀላቀሉም ምክንያት ሆኗል። ይህንን ውጤታማነት አሁን ወደ ግል ይዞታ በሚተላለፉት ዘርፎች ላይ መድገም ይቻላል ወይ የሚለው ግን ጥያቄ ይነሳበታል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይን ጨምሮ ሌሎች አዲሱን አቅጣጫ የሚደግፉ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በከፊል ወደ ግል መዘዋወራቸው አገልግሎት እንዲቀላጠፍያደርጋል ተደራሽነትንም ይጨምራል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com