“በሐረር ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት 650 ሔክታር መሬት ተዘርፏል”

Views: 219

አብዱላኪም ዮኒስ የሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ

አብዱላኪም ዮኒስ ይባላሉ። ከለውጡ በኋላ የሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ደንብ ማስከበር፣ የመሬት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሴፍትኔት ፕሮግራም፣ ማዕድንና ኢነርጂ፣ የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን፣ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ድርጅቶች እሳቸው በሚመሩት ተቋም ውስጥ የታቀፉ ናቸው። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ወደ ሐረር በማቅናት በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአብዱላኪም ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ባለፉት ስድስት ወራት በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ፣ ሰፊ የሆነ የመሬት ወረራ መካሔዱ ይነገራል። አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎችንም ከገዛ ቤታቸው በማስወጣት ቤቱን ለራሳቸው ያደረጉ ኀይሎች አሉ የሚባል ነገር ሰምተናል። ይህ ምን ያክል እውነት ነው? የክልሉ መንግሥት ምን እርምጃ ወስዷል?
አብዱላኪም፡ ያነሳኸው ነገር እውነት ነው። ባለፉት ስድስት ወራት 650 ሔክታር መሬት በተደራጁ ኀይሎች ተዘርፏል፤ ከአንድ ሺሕ በላይ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል፤ ሃረማያ ዩኒቨርስቲ ፍራፍሬ የሚያመርትበት ሴራት ፓርኪንግ ተዘርፏል፤ ቤተ ክርስቲያንና መስጊዶች ተደፍረዋል። የሚሰግድበትን መሲጊድ ደፍሮ ቤት የሠራ አለ፤ በርካታ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተቀምተዋል፤ ገንዘብ ቆጥበው ኮንዶሚኒየም ቤት የሠሩ መምህራንና ሠራተኞች ለአንድ ዓመት ተኩል ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገው፣ በቤቱ ሌሎች ሰዎች ይኖሩበት ነበር።

ችግሩ ይሔ ብቻ አልነበረም፣ ሕገ ወጥ ቤቶች እየተሠሩ በዩኔስኮ የተመዘገቡት ቅርሶችም አደጋ ላይ እየወደቁ ነው። ጀጎል ውስጥ ፓርኩ አካባቢ ሕገ ወጥ ግንባታዎች በመስፋፋታቸው ለፓርኩ አደጋ ሆነዋል።

የክልሉ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከዓመት በኋላ ሕገወጦቹን በማስወጣት የቤት ባለቤቶቹ እንዲገቡ ተደርጓል። እነዚህ በፖለቲካ ኀሎችና በአንዳንድ የጸጥታ አካላት ተታለው ሕገ ወጥ ወደሆነ ተግባር የገቡት ሥራ አጥ ወጣቶች፣ ከዚህ ቀደም ሕጋዊ መንገድ ስላልተዘጋጀላቸው ሕገ ወጥ መንገድን እንደ አማራጭ ሲጠቀሙ ተስተውሏል።

መንግሥት የወጣቶቹን እርምጃ በኀይል ከማስቆም ይልቅ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል የማኅበር ቤት ተዘጋጅቶላቸው ፕላን ተሰርቶ፣ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው የባንክ ብድር እንዲያገኙ ነው ያደረገው። ምክንያቱም ችግሮችን በኀይል ለመቅረፍ መሞከር የሚያመጣውን ችግር ከዚህ በፊት አይተነዋል።

ይህ ሁሉ ችግር ሲከሰት የጸጥታ አካላት አልነበሩም? በቀጣይስ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር እንደማይፈጸም ምን መተማመኛ አለ?
የጸጥታ አካላቱም የወንጀሉ ተባባሪዎች ነበሩ። ሕዝቡን በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ በመከፋፈል፣ የጸጥታ ችግር በክልሉ እንዲፈጠር በማድረግ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። በዚህም ሳቢያ በርካታ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ከተጣራ በኋላ ብዙዎቹ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። በወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩትም በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል።

ለሁሉም ሕጋዊ መንገድ አዘጋጅተንላቸዋል። ከዚህ በኋላ በሕጋዊ መንገድ የሚያልፈውን ድጋፍ እያደረግን እናበረታታለን፤ ከሕጋዊው መንገድ ወጥተው ለሚሔዱትን ግን እስከዛሬ እንዳደረግነው በልምምጥና በልመና የምናልፈው አይሆንም፤ ሕግን ተላልፎ የሚገኝ በሕግ ይጠየቃል።

ከተማዋ ቆሻሻ መድፊያ አጥታ ለችግር መዳረጓ ይታወቃል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ካሳ ተከፍሏል ይባላል፤ ይሁንና ችግሩ ግን እንዳልተቀረፈ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህ ላይ የእርሶ ቢሮ ምን ምላሽ አለው?
እውነት ነው፤ የከተማውን ቆሻሻ መጣያ ሥፍራ እንዳንጠቀምበት የአካባቢው ማኅበረሰብ በመከልከሉና ካሳ በመጠየቁ ምክንያት፣ ለአንድ ወር ያህል በከተማዋ ቆሻሻ መጣያ ጠፍቶ፣ ከተማዋ ሸትታ ነበር። ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ሰዎችም ተቃውሟቸውን በሰልፍ እስኪገልጹ ድረስ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖም ነበር።

የዛሬ 10 ዓመት ከሐረር ከተማ 7 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ [በተለምዶ]‘ላንድ ፊል’ የምትባል ሥፍራ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለ10 ዓመት የሚሆን ካሳ ተከፍሏቸው፣ 13 ካሬ ሜትር በሚሆን ቦታ ላይ ቆሻሻ እንዲጣል ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ለአርሷደሮቹ ተረፈ ምርቱ ለማዳበሪያ ምርት እንደሚሆንና ፕላስቲኮቹም ለፕላስቲክ ምርት ውለው የአካባቢውን ማኅበረሰብ እንደሚለውጡ ተነግሯቸው፣ በአካባቢው ቆሻሻ መጣል ይጀመራል።

ከ10 ዓመት በኋላ በአካባቢው የሚጣለው ቆሻሻ እየሸተተ በመምጣቱና አካባቢውንም በመበከሉ፤ ይመረታል የተባለው ማዳበሪያም ሆነ ሌላው ነገር ምርት ላይ ውሎ ባለመታየቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ በቂ ካሳ አልተከፈለንም፣ የሐረርን ቆሻሻ አንሸከምም፣ የጉዳት ካሳም እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበው በተደራጁ ወጣቶች የከተማው ቆሻሻ እዛ ቦታ ለይ እንዳይጣል ተከለከለ።

ችግሩ እየከፋ በመምጣቱ በመጀመሪያው ዙር 16 ሚሊዮን ብር በመክፈል እፎይታ አገኘን። ከወራት በኋላ በኹለተኛ ዙር ራቅ ብሎ የሚኖረው ገበሬ እኔም ቆሻሻው ሸቶኛል፤ ስለዚህ የጉዳት ካሳ እፈልጋለሁ በማለት ጥያቄውን አቀረበ። በተመሳሳይ ጊዜ የመሬት ባለቤት ነን የሚሉ አምስት ሰዎች የመሬት ካሳ እንፈልጋለን ብለው መጡ።

በኹለተኛው ዙር ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፍለን ቆሻሻው እንዲደፋ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛው የካሳ ክፍያ ይሔ ነው።

የእነዚህ ሰዎች ጥያቄ ሕጋዊ መሆኑን ተቀብላችሁ ነው ወይስ ክልሉን ለማረጋጋት የካሳ ክፍያውን የፈጸማችሁት? አንዳንድ ወገኖች ከዚህ በስተጀርባ የባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት ሲናገሩ ይደመጣል። ይህ ነገር ምን ያክል ትክክል ነው?
ይሔ ሁሉ መዘዝ ባለፉት 27 ዓመታት መሬት የመንግሥት ነው፤ ሕዝብ ምን አገባው በሚል የተወሰደው እርምጃ ያመጣው ጦስ ነው። ብዙ ነገሮች ይከናወኑ የነበሩት በሕዝቡ ፈቃድ አልነበረም። በዚህም አርሶ አደሩ ቂም ይዟል። በተመሳሳይ በአካባቢው እየተበራከተ የመጣው ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ክፍተቶችን እንደ አጋጣሚ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። በሐረሪ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች የተስተዋሉ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ካሳ መክፈላችን አማራጭ የሌለው ነገር ነበር።

የባለሥልጣናት እጅ አለበት ለሚለው በማስረጃ ተደግፎ እስካልቀረበ ድረስ አሉባልታ ነው የሚሆነው። አሁን ያለው አመራር ከተሾመ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ አዲሱ አመራር ክልሉን በማረጋጋት ሐረር የመዝናኛና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን በመሥራት ላይ ነው የሚገኘው። ካለፉት ስድስት ወራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆኑ መሻሻሎች በክልሉ እየታዩ ነው የሚገኘው።

ይሔ ችግር ከተቀረፈ በኋላም በተመሳሳይ ወደ ከተማዋ የመጠጥ ውሃ እንዳይገባ መደረጉንም ሰምተናል፤ ምክንያቱ ምንድን ነበር? የተወሰደውስ እርምጃ?
ሐረሪ ውሃ የምታገኘው ከድሬዳዋ 75 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አዶሌ፣ አዎዳይንና ሃረማያን አቋርጦና አዳርሶ የተረፈውን ነው። ይሄንን የውሃ መስመር በኦሮሚያ ክልል ሃረማያ ላይ በመዝጋት “10 ሚሊዮን ብር ወደ አካውንታችን ካላስገባችሁ በውሃ ጥም ታልቃላችሁ” የሚሉ ኀይሎች ተነሱ፤ ጉዳዩን ለሚመለከተው የኦሮሚያ ክልል አሳውቀን፤ የክልሉ መንግሥት “ይህ ስርዓተ አልበኝነት ነው መቆም አለበት” ብሎ በወንጀለኞቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ ቁልፉን እንዲያስረክቡን አድርጓል።

ብዙም ሳይቆይ የክልሉን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ኤረር በሚባል አካባቢ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት ተቋቁሞ፣ ተመርቆ ሥራውን በጀመረ በአምስተኛው ወር “በእርሻ ቦታችን ላይ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ሲወጣ ድርቀት አምጥቶብናል፣ እርሻችንን በመስኖ ውሃ ማጠጣት አልቻልንም፣ ካሳ አልተከፈለንም” በሚሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ውሃው እንዲቋረጥ ተደረገ፤ የመብራት መስመሩንም በጣጠሱት። ከአካባቢው ሰዎች ጋር በተደረገ ድርድር መሰረት “ንጹሕ የመጠጥ ውሃ በየሰፈራችን ይግባልን፣ መብራት ይግባልን ይሔ ካልተሟላልን ውሃውን እንለቃለን” በማለታቸው ለውሃ ፕሮጀክት 8 ሚሊዮን ብር ከፈልን፤ [ተጨማሪ] 15 ሚሊዮን ብርም የካሳ ክፍያ ተፈጸመ። በአጠቃላይ ለመልሶ ማልማት ብቻ 59 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፍለናል።

እነዚህ ነገሮች ስላለመደገማቸው ምን ዋስትና አለ? ችግሮቹንስ በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?
በአገራችን ሰማንያ ከመቶ አርሶ አደር ሃያ ከመቶ የሚሆነውን ከተሜ መመገብ አልቻለም። አብዛኛውን የከተማችን ነዋሪዎች ከድኅነት ወለል በታች በመሆናቸው የምግብ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ናቸው። የወጣት ሥራ አጥ ቁጥሩም በእጅጉ ጨምሯል፤ ስለዚህ ግርግር ሲፈጠር ወጣቱ አጋጣሚውን በመጠቀም ችግር ሊፈጥር ይችላል።

ስለዚህ መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። ያንንም ለማድረግ በ2011 በጀት ዓመት 118 ሚሊዮን ብር በመመደብና ለወጣቱ ብድር በማዘጋጀት በማኅበር ተደራጅቶ እንዲሠራ ተደርጓል። ባጀቱ ለአንድ ዓመት ብቻ የተመደበ ነው። በየዓመቱ ይህንን በማሻሻል ወጣቱ እራሱን በሥራ እንዲወጥር እያደረግነው ነው።

የባለቤትነት ሥሜት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ማስተካከል ያስፈልጋል። ወጣቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው መሥራት ባለመቻላችን የራሱን ንብረት ሲያቃጥል፣ ሲመዘብርና ወገኑን ሲያንገላታ ከርሟል። የአመጽ ውጤት ሆኖ የምናየውም ለዚህ ነው። በዚህ ላይ በስፋት ለመሥራት ዕቅድ ይዘን መንቀሳቀስ ጀምረናል።

ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን ሰላምና ሕግን የማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ ይገኛሉ። ሁሉም ነገር መስመሩን እየያዘ ይገኛል። ከዚህ በኋላ ግን ተመሳሳይ ድርጊቶችን ለመፈጸም በሚሞክሩ አካላት ላይ ትዕግስት አይኖረንም። የሚገዛን ሕግና ሕግ ብቻ ይሆናል። ክልሉ ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት የሠላም መዲናነት እንዲቀጥል ሁሉም አካላት ተባብረው በመሥራት ላይ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com