ቢ ጂ አይ ዘቢዳር ቢራን ጠቀለለ

Views: 809
  • የሸማቾች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን ውሕደቱ እስኪያፀድቅ እየተጠበቀ ነው

ከዚህ ቀደም የዘቢዳር ቢራን 60 በመቶ ኪፓሪ ከተባለው የሞሪሸስ ድርጅት የገዛው ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ ቀሪ 40 በመቶውን ከጀማር ሁለገብ ኢንዱስትሪ መጠቅለል መቻሉ ታወቀ።

ሁለቱ ድርጅቶች ሽያጩ ላይ መግባባት ላይ ቢደርሱም ስምምነቱ በሸማቾች መብት ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን ተመርምሮ እስኪፀድቅ ድረስ የውሕደት ሒደቱ ተግባራዊ ያለመደረጉም ተውቋል። ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ገበያ የገባው ዘቢደር ከ350 ሺህ ሄክቶ ሊትር በላይ ቢራ የማምረት አቅም ሲኖረው ስምምነቱ ቢ ጂ አይ አቅም ወደ 4.6 ሚሊየን ሄክቶ ሊትር ያሳድገዋል።

በኢትዮጵያ የግል የቢራ ፋብሪካ ቀዳሚ የሆነው ቢ ጂ አይ የዘቢዳርን አብላጫ ሼር ይዞ የነበረውን የኪፓሪ እናት ድርጅት ዩኒብራ የሼር ድርሻውን ለካስትል ለማስተላለፍ በመስማማቱ በኢትዮጵያ ለተደረገው ስምምነት መሰረት መሆኑ ይታወሳል።
በመጀመሪያ የገዛውን እና በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የቢራ ማምረቻ ፋብሪካውን በመመስረት ወደ ሥራ የገባው ቢ ጂ አይ ካስትል እና ባቲ በተባሉት ምርቶቹ ወደ ገበያ ገብቷል። በመቀጠልም በ10 ሚሊዮን ዶላር አንጋፋውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ከመንግሥት በመግዛት እና ለማስፋፊያ እና ለዕድሳት አንድ ቢሊዮን ብር በማውጣት አቅሙን አሳድጓል።

የሐዋሳ ፋብሪካውን በማስመረቅም በገቢው ላይ የነበረውን ድርሻ ከፍ በማድረግ በዓመት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር የማምረት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በኋላም 350 ሺህ ሄክቶ ሊትር የማምረት አቅም የነበረውን ራያ ቢራን በተለያዩ ደረጃዎች ድርሻ በመግዛትና በመጨረሻም ሙሉ ለሙሉ በመጠቅለል የማምረት አቅሙን አሳድጓል።

የቅርብ ተፎካካሪው ሄኒከን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ከገባ እና በተለይም የቂሊንጦ ፋብሪካውን መገንባት ከጀመረ በኋላ በአገሪቱ ትልቁ የቢራ አምራችነት ደረጃውን ላለማስነጠቅ የተለያዩ የመጠቅለል እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል። የቢራ ገበያውን በቅርብ ጊዜ ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ የሆነው ሄኒከን በቂሊንጦ ያስገነበው ፋብሪካ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የምርት መጠኑን አምስት ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ማሳደጉ ይታወሳል።

ቢ ጂ አይ ዘቢዳርን ለመጠቅለል ባደረገው በዚህ ስምምነትም ለገበያ ድርሻው ካለው አስተዋፅኦ ባሻገር በመላው አገሪቱ ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግ በማለም እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለፅ እንደነበር ይታወሳል።

ቢ ጂ አይ እና ዘቢዳርም ውሕደታቸው እንዲፈቀድላቸው ማመልከታቸውን ከባለሥልጣኑ የተገኘነው መረጃ የሚያሳይ ሲሆን ባለሥልጣኑም የኹለቱ ድርጅቶች ውሕደት በፍትሐዊ ውድድር ላይ የሚኖረውን ጫና እንዲሁም አጠቃላይ የውሕደቱን አካሔድ በማጥናት ላይ ይገኛል።

የሸማቾች መብት ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን በተቋቋመበት አዋጅ መሰረት ማንኛውም ዓይነት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የውሕደት ሒደቶችን አይቶ የመመርመር ሥልጣን ያለው ሲሆን ያለ ባለሥልጣኑ ይሁንታ የሚደረግ ውሕደትም ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com