ትንሳኤ የራቀው ፖለቲካ!

Views: 410

ይህ ሳምንት ለክርስትና እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ትንሣኤ የተከበረበት ነው። ይናገር ጌታቸው ይህንን ሃይማኖታዊ ትውፊት ተንተርሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከወደቀበት ትንሣኤ ማግኘት የተሳነው ለምንድ ነው በማለት የጻፉትን ኹለተኛ እና የመጨረሻ ክፍል እነሆ።

(ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)
ዐፄ ቴዎድሮስን ተከትለው የነገሡ ስድስት መሪዎች በዚህ ቦይ ፈሰዋል። ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር ከተፈለገ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት አስፈላጊ ነው ተብሎ ብዙ ተሠርቶበታል። ባለፈው አንድ መቶ ዓመት ታሪካችን ውስጥ ከግማሽ የዘለለው የንግሥና አገዛዝ የሚስተዋልበት ነበር። ይህ ደግሞ በሕዝብና በመንግሥት መካካል ያለው ግንኙነት እየዘመነ እንዳይሔድ እንቅፋት ሆኗል። ለዚህ በመርስዔ ሐዘን ወልደቂርቆስ የኻያኛው ዘመን መባቻ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝን አንድ ታሪክ አብነት አድርጎ ማለፍ ተገቢ ይመስለኛል። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ጅግጅጋ አምርተው የአካባቢውን ነዋሪ ይሰበስባሉ። በውይይቱም በልማት አልተጠቀምንም የሚል ስሞታ ተደጋግሞ ይቅርብላቸዋል። በዚህ ወቅት ንጉሡ የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነበር። “መጀመሪያ አማርኛ ቻሉ ካዛ ጥያቄያችሁን አቅርቡ” የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲህ ያለ ምለሽ በመንግሥትና በዜጎች መካካል ያለው ግንኙነት ያኔም እንደቀደመው ዘመን መሆኑን ያስገነዝባል።

በዚህ ምክንያትም ፖለቲካችን ከመሻሻል ይልቅ በነበረበት ቀጠለ። ራሱን ከማደስ ይልቅ ባለበት አዘገመ። ይህ ደግሞ ንጉሣዊው ስርዓት በብሔር ፖለቲከኞች እየተጠላ እንዲሔድ በር ከፈተ። ሪቻርድ ግሪን ፊልድ ከ1953 የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ኦሮሞዎች ለብቻቸው ሌላ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ አሲረው ነበር ይሉናል። ኦላና ዞጋ “ግዝትና ግዞት” በተባለ መጽሐፋቸው በ1950ዎቹ መገባደጃ በጄኔራል ታደሰ ብሩ የተመራ የግድያ ሙከራ በንጉሡ ላይ ለማካሔድ ቢታሰብም እንደከሸፈ ይነግሩናል። ዶናልድ ሌቪን በአንፃሩ በዊንጌት ትምህርት ቤት የነበሩት ተማሪዎች በብሔር ተቧድነው ረብሻ አስነስተው እንደነበር ያስታውሱናል። እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንሳኤ ሌላ ኀልዮታዊ አማራጭ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ነበሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካካል ያለው የፖለቲካ ተቃውሞ መልኩን የቀየረውም በዚህ ገፊ ምክንያት የተነሳ ይመስላል። በ1962 ዋለልኝ መኮንን “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” የተሰኘ ጽሑፉን ይዞ ሕልማችን ይህ መሆን አለበት አለ።ሰሜኑን ብቻ የምትጠቅም ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልትባል አይገባትም ሲልም ተከራከረ። በፍጥነትም በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተች አገር የመመሥረት ግዴታ አለብን አለ። የዐፄ ቴዎድሮስን የፈረስ ሥም በተዋሰው “ታጠቅ ” መጽሔት የቀረበው ይህ ሐሳብ በወቅቱ ትልቅ መነጋጋሪያ ለመሆን አፍታ አልወሰደበትም። አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) “ምሁሩ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ዋለልኝ ሐሳቡን ሲያቀርን በአዳራሹ የታደመው ሰው ስሜት የተመሰቃቀለ እንደነበር ራሳቸውን ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ።

ይህ ድብልቅልቅ ስሜት ግን በጊዜ ሒደት እየጠራ ለፖለቲካችን ትንሳኤ የብሔር መብትን የሚያስከብር ስርዓት ኅልውና አስፈላጊ ተደርጎ ተቆጠረ። ዐፄ ቴዎድሮስ የሚመኟትን አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ የመመሥረት ሕልምም ግቡን የሚመታው በብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያምን ስርዓት ሲመሠረት ብቻ ነው የሚል አቋም በየቦታው ናኘ። የብሔር ጥያቄም በጊዜው በነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተካተተ። በዘመን ሒደትም አንጋፋው የብሔር ድርጅት ሕወሓት ለሥልጣን በቃ።

ሀብታሙ አለባቸው “ታላቁ ተቃርኖ” በተባለ መጽሐፋቸው ይህን ሒደት በተመለከተ ጥያቄዎችን ለአንባቢያን ይወረውራሉ። የመጀመሪያው ሐሳብ የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ አንገብጋቢ ከነበር ለምን የሕወሓት ትግል 17 ፈጀ? የሚለው ነው።ሌላው ሕወሓት የሰሜን ኢትዮጵያ አካል ሆና እያለ እንዴት የብሔር ጭቆናን አጀንዳዋ አደረገች ይላል። ኹለቱ ጥያቄዎች እራሳቸውን የቻሉ የምርምር ሐሳቦችን የማመንጨት አቅም ቢኖራቸውም ከተነሳሁበት ነጥብ አንፃር ግን ጥቅል ምለሽ ሰጥቼ ልለፍ። ሕወሓት አነሳሱ ሶሻሊስታዊ ስርዓትን ለመመሥረት እንደ ነበር የሚታወቅ ነው። ሶሻሊዝም ደግሞ መደብን መሣሪያ ያደረገ ትግል የሚካሔድበት ሜዳ ነው። ሕወሓት ከዚህ አንፃር የሚታገልለት መደብ የማግኘት ፈተና ከፊቱ የተጋረጠ ድርጅት ነበር። በዚህ ምክንያትም ትግሉን ለማቀጣጠል የብሔርን ጉዳይ የመደብ ሚና እንዲኖረው አደረገ። ሰሜን ኢትዮጵያን በዳይ ባደረገ የብሔር ፖለቲካ ትግራይን ነጥሎ ተብዳይ አድርጎ ትግሉን ቀጠለ። ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በዚህ ሒደት ተጉዞ አገረ መንግሥቱን ተቆጣጠረ። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ትንሳኤ ያረጋግጣል የተባለው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የማክበር ጉዳይም በሕገ መንግሥት ደረጃ ፀደቀ።

ኢትዮጵያ የተያያዘችው አዲሱ ስርዓት በመንግሥትና በሕዝብ መካካል ያለውን ግንኙነት በማዘመን ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሎ ቢጠበቅም ውጤቱ ግን የታሰበውን ያህል አልነበረም። ለዚህ ደግሞ ኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች ያሉ ይመስላል። የመጀመሪያው የአገሪቱ ፖለቲካ ትርክር ሲሆን ኹለተኛው ፍትሐዊ ስርዓትን ማስፈን አለመቻሉ ነው። የአገሪቱ ፖለቲካ ባሕል ከሞላ ጎደል በሰሜን ፖለቲከኞች የሚዘወር ነው። ይህ ደግሞ የደቡብ ፖለቲከኞች በአገራቸው ባይተዋርነት እንዲሰማቸው አድርጓል። የሕዝባችንን ጥቅም የምናስከብረውም ከኢትዮጵያ ከተገነጠልን ብቻ ነው የሚል ፅንፈኝነትን ወልዷል። የሰሜን ኢትዮጵያ ፖለቲካ ባሕል የደቡብ ፖለቲከኞችን አግልሎ እራሱን ያዋሐደ አይደለም።

የአማራና ትግራይ ፖለቲካ ልኂቃን የሥልጣን ይገባኛል ልማድ የተጠናወታቸው ናቸው። በዚህ ምክንያትም አንዱ የያዘው ሥልጣን ለሌላው የሚዋጥ አይደል ። የብሄርን ፖለቲካን ተንተርሶ ይመጣል የተባለው የፖለቲካ ትነሳኤ የከሸፈው ግን በዚህ ምክንያት ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የተከተለችው የብሔር ፖለቲካ የፍትሐዊ ተጠቃሚን ጥያቄ የሚነሳበት ነበር። ፍትሐዊ ስርዓት አለመኖሩ በሕዝቦች መካካል መጠራጠር እንዲሰፍን ዕድል ፈጥሯል። የኹለቱ ነገሮች ድምር ውጤት ደግሞ አገር መንግሥቱን ወደ መገዳደር ከፍ ብሏል። በዚህ ሒደትም ኢትዮጵያ የፖለቲካ ትንሳኤዋን ማምጣት አይደለም የተያያዘችውን መንገድም ልትቆየበት አዳግቷታል።

የፖለቲካ ትንሳኤውን እንዴት እንፍጠር?
የአገራችን ፖለቲካ ትንሳኤ ከላይ ከፍ ብዬ አንደገለጽኩት የሚቀዳው ከኀልዮትና ከገቢር ነው። ኀልዮቱ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያከበረች አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ መፍጠር ነው። ይህ ፍላጎት በእስካሁኑ ሒደት አልተሳካም። አለመሳካቱ ግን የውድቀታችን አልፋና ኦሜጋ አይደለም። የነገ መንገዳችን እንዲሠመር ፖለቲካችን ትንሳኤ እንዲኖረው ወሳኙ ነገር ብሔራዊ ባሕል (National culture) እንዲኖረን መጣር ነው። ብሔራዊ ባሕል መፍጠር ሲቻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘውጋዊ ማንነቱን ትቶ ወደ አገራዊ ማንነቱ ይመጣል። ተመሳሳይ አገራዊ ርዕይም ይኖረዋል። ኢትዮጵያ የሚለው አገራዊ ሥዕለ ሕሊናም በሁላችንም ውስጥ ያለው መልክ ተቀራራቢ ይሆናል። እንዲህ ያለው መቀራረብ ታዲያ የዜጎች አገራዊ ፍላጎት ከአንድ ጅረት እንዲቀዳ ዕድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ ባሕል ትፍጠር ማለት ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተጨፍለቀው ወደ አንድ ቋንቋ እና አንድ ሃይማኖት ትርክት ይመለሱ ማለት አይደለም። ብሔራዊ ባሕል መገንባት የሚቻለው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው። እዚህ ላይ መሠረታዊው ጥያቄ ለአንድ ብሔራዊ ባሕል ማበብ የሚረዳው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር እንዴት ሊሳካ ይችላል የሚለው ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የጋራ ፖለቲካዊ ባሕል ሊገነባ የሚችለው ሁሉም ዜጋ ዘብ የሚቆሙለት ሕገ መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊያን የሚሰበሰቡበት የጋራ የፖለቲካ ዋርካ ሳይኖራቸው ፖለቲካዊ ትንሳኤን ሊያልሙ አይችሉም። የአማራ ፖለቲካ ልኂቃን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አይወክለኝም ሲሉ የቀረው ከዚህ ሕገ መንግሥት ላይ አንድ አንቀፅ ቢነካ አገር ይፈርሳል እያለ የሚመጣ ፖለቲካዊ ትንሳኤ አይኖርም።በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሟገትለትን ሕገ መንግሥት እንዲኖረን ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል።

ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን መፍጠር ነው። የአገራችን የእስከዛሬ ታሪክ እንደሚያሳያው የሰሜኑንም ሆነ የደቡብን፣ የምዕራቡንም ሆነ የምሥራቁን ሕዝብ እኩል ተጠቃሚ ያደረገ የኢኮኖሚ ስርዓት መፍጠር አልተቻለም። በዚህ ምክንያትም የኢኮኖሚ ፍትሐዊነት ጥያቄ አሁንም አንገብጋቢ እንደሆነ ይገኛል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ችግር በኹለት መንገድ ሊፈታ የሚችል ነው። አንደኛው መንገድ ያለውን ውስን ሀብትና ዕድገት ፍታሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ሲሆን ኹለተኛው ፍኖት ፈጣን ዕድገትን በማስመዝገብ ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር ነው።

ካርል ማርክስ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠርን አስፈላጊነት በቀላል ምሳሌ እንዲህ ይገልጸዋል። አንድ ጆንያ ድንች ተቋጥሮ ቢቀመጥ የተፈታ ዕለት መበታተኑ አይቀርም። ይህ እንዳይሆን ግን ድንቹን ፋብሪካ ውስጥ አስገብቶ አንዱን ከአንዱ ማዋሃድ ያስፈልጋል። ብዝኀ ባሕል ያላት ኢትዮጵያ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረስብ እስካልፈጠረች ድረስ በጆንያ ታስሮ ከተቀመጠው ድንች ጋር የምትመሳስል ናት። በመሆኑም በዚች አገር ፈጣንና ፍታሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በብሔሩ ሳይሆን በኢንዱስትሪው ዙሪያ የሚሰባሰብ ዜጋ ማፍራት ያስፈልጋል። ይህን ስናደርግ የዜጎች ጥያቄ በየፋብሪካዎቹ የሚከፈላቸው የደሞዝ ሁኔታ እንጅ የብሔር ጉዳይ አይሆንም።

ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ትነሳኤ ስናወራ ያለፈውን አገራዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ነገ የሚገጥመንንም ታሳቢ ማድረግ አለብን። ጆን ማርካኪስ ስለቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስጋት መላምቱን ሲሰነዝር የመሐልና የዳር አገሩ የፖለቲካ ልዩነቱ ቀጣይ ስጋት ሊሆን ይችላል ይላል። በርግጥም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰብክ ሰው የአንድ ጋምቤላ እናት ሕይወት ካላሳሰበው የውሸት ኢትዮጵያዊነት ተጠናውቶታል ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት ያለው የአገራችን ፖለቲካ ከዚህ እውነት የሚርቅ አይደለም።አማራም ይሁን ኦሮሞ ትግሬም ይሁን ሲዳማ ለአገራዊ የፖለቲካ ትንሳኤ እሠራለሁ ቢልም ከእርስ በርስ ጉተታ አልተላቀቀም። ማርካኪስ የነገዋ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ጤናማ እንዲሆን ከተፈለገ ለዚህ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ።

እርግጥ ነው የአገራችን ፖለቲካ ትንሳኤ የኢትዮጵያዊነትን ጭንብል ከመልበስ ወጥቶ እውነተኛ ፈተናዎችን በመጋፈጥ የሚገኝ መሆኑ አያከራክርም።

የአገራች ፖለቲካ ትንሳኤ አልባ የሚባል አይደለም። ግን ደግሞ ለትንሳኤ የሚያበቁ ነገሮቹ ጋና አልተጀመሩም። በመሆኑም የሁላችንም ሕልም የሆነውን የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረባት አንዲት ጠንካራ አገር ለመመሥረት የየራሳችንን ጡብ ማኖር አለብን።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com